በደቡብ ክልል ከ720 ሺሕ በላይ ሴቶች የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ ነገ ይጀምራል

ሚያዝያ 5/2014 (ዋልታ) በደቡብ ክልል ከ720 ሺሕ በላይ ሴቶች የሚሳተፉበት ክልል ዐቀፍ የውይይት መድረክ ከነገ ጀምሮ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

መድረኩ በብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ በተቀመጡ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ላይ ግልጽነት መፍጠር የሚያስችልና የጉባኤውን ሀሳቦች የሚያዳብር ነው ተብሏል፡፡

የውይይት መድረኩ በ157 የደቡብ ክልል ከተሞች የሚካሄድ ሲሆን ከአጠቃላይ መድረኮቹ 22ቱን የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ ሴት አመራሮች እንደሚመሯቸው ተገልጿል፡፡

የደቡብ ክልል ሴቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ነኢማ ሙኒር በውይይት መድረኮቹ የክልሉ ሴቶች የሚያነሷቸው የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ የሚፈቱበትና በችግሮቹ መፍትሄዎች ላይ ሴቶችን ዋና ተዋናይ ለማድረግ ከጋራ መግባባት የሚደረስበት ይሆናል ብለዋል፡፡

ከውይይት መድረኮቹ ጎን ለጎን የኑሮ ውድነቱን ማቃለል የሚያስችል “ምግቤን ከጓሮዬ ጤናዬን ከምግቤ” የሚል የከተማ ግብርና ይፋዊ የማስጀመሪያ ፕሮግራም እንደሚካሄድ ከደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡