በኢትዮጵያ የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው

ሚያዝያ 7/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የልጅነት ልምሻን ለመከላከል የሚያስችል ክትባት እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት እየተሰጠ ነው።

በአማራ ክልል ለሁለተኛው ዙር እየተሰጠ ባለው የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት ከደቡብ ወሎ፣ ከሰሜን ወሎ ፣ ከደሴ ከተማ አስተዳደርና ከዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ውጭ ባሉ አካቢዎች እየተሰጠ ነው፡፡

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በመጀመሪያው ዙር የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት በክልሉ ያሉ ክትባቱ ከሚያስፈልጋች ህጻናት 98 በመቶ መሸፈኑን ገልጸው በሁለተኛው ዙር የክትባት መርሃ ግብር ለ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት እንደሚከተቡ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በሀረሪ ክልል ሁለተኛው የፖሊዮ ክትባት መሰጠት ተጀምሯል::

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኢብሳ ሙሳ በክልሉ በሚሰጠው የክትባት ዘመቻ ከ56 ሺሕ 300 በላይ የሚሆኑ ህፃናትን ለመከተብ መታቀዱን ገልፀዋል።

በመሆኑም ኅብረተሰቡ ከ5 አመት በታች ለሆኑ ህፃናት በማስከተብ የፖሊዮ በሽታ ለጥፋት በሚከናወኑ ተግባራት ሚናውን እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በጋምቤላ ክልልም በተመሳሳይ የልጅነት ልምሻ ክትባት እየተሰጠ ሲሆን ለ4 ቀናት በሚቆየው የክትባት መርሃ ግብር በሁሉም የክልሉ ወረዳዎች ከ88 ሺህ በላይ ሕፃናት ይከተባሉ ተብሏል።

በክልሉ ባሉ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ደግሞ 53 ሺሕ የሚደርሱ ሕፃናት እንደሚከተቡ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አስቻለው ዓባይነህ በመጀመሪያው ዙር የልጅነት ልምሻን ለመከላከል የሚያስችለው ክትባት በአማራና በአፋር ክልሎች በወረራ ስር ከቆዩ አካባቢዎች ውጭ መሰጠቱን ለአሚኮ ተናግረዋል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በመላ ሀገሪቱ ለ16 ሚሊዮን 748 ሺሕ 200 ሕፃናት የልጅነት ልምሻ ክጽባት መሰጠቱን ገልጸዋል።