የሰሞነ ሕማማት ኃይማኖታዊ ትርጓሜ

በአመለወርቅ መኳንንት

ሚያዝያ 10/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የታላቁ የሁዳዴ ወይንም የዓብይ ፆም መገባደጃ ሳምንት ሰሞነ ሕማማት ይባላል፡፡

በመሆኑም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህን ከትንሣኤ በፊት ያለው አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት /የሕማማት ሳምንት/ በማለት ትዘክረዋለች።

ሕማማት የሚለው ቃል “ሐመ”፣ “ታመመ” ከሚለው የግዕዝ ግስ የወጣ ሲሆን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማሙና ሞቱ የሚዘከርበት ሳምንት ነው።

                                                  ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ

ሀመ – ማለት ታመመ ማለት ሲሆን ይህም የሰውን ዘር ሁሉ ከዲያቢሎስ ባርነት ነፃ ለማውጣት ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ የተቀበላቸው መከራዎች የሚታሰብበት ቀን መሆኑን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ ይገልፃሉ፡፡

በዚህም የሕማማት የመጀመሪያ ቀን ሰኞ የሚታሰበውና የሚዘክረው የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ በቸልተኝነት እንዳይደክም፣ እንዳይጠወልግ፣  ወደ እሳትም እንዳይጣል የሚታሰብበት ቀን በመሆኑ አንጾሖተ ቤተ መቅደስ እና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት መሆኑን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡

የእምነቱ ተከታዮችም በሰሞነ ሕማማት የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት የሚያለቅሱበት ከሌሎች ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ አምላካቸውን የሚማፀኑበት ጠዋት ማታ ደጅ የሚጠኑበት እና በስግደት የሚያሳልፉት ሳምንት እንደሆነ የእምነቱ አባቶችም ያስተምራሉ፡፡

የታላቁ የዓብይ ጾም የመጨረሻ ሳምንት በሆነው ሰሞነ ሕማማት የክርስቶስ ህማም የሚታወስበት በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ሳምንት ነው፡፡ ሰሞነ ሕማማት የዓመተ ኩነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ሰኞ የበለስ ቅጠልን ተመልክቶ ምንም ፍሬ ባለማግኘቱ ካሁን ጀምሮ ለዘላለም ምንም ፍሬ አያፍራብሽ ብሎ የረገመበት የበለሱ ዛፍ ምሳሌ የተለየ ሃይማኖታዊ ትርጓሜ እንዳለው አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ አክለው ይናገራሉ፡፡