ተዳክሞ የቆየውን የቱሪዝም ዘርፍ ማነቃቃት እንደሚገባ ተገለፀ

ሚያዝያ 11/2014 (ዋልታ) በዓለም ዐቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በአገሪቷ ወቅታዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት የተዳከመውን የቱሪዝም ዘርፍ ማነቃቃት እንደሚገባ ተገለፀ።

ይህን መሰረት ያደረገ ለሁለት ቀናት የሚቆይ የስልጠና መድረክ በቱሪዝም ሚኒስቴር እና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አዘጋጅነት እየተካሄደ ሲሆን የፌዴራል እና የክልሉ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ የቱሪዝም መስህብ መዳረሻዎች ውስጥ ቀዳሚ የሆነችው ላሊበላ ከተማ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ካስከተለባት የቱሪዝም መዳከም በተጨማሪ በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነት ክፉኛ እንዳደከማት ተናግረዋል።

ዘርፉ ከፍተኛ የሀብት ምንጭ ቢሆንም እንደ ሀገር ከነበረበት ክፍተት በተጨማሪ በተለይም በክልሉ በተፈፀመ የአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ምክንያት የውጭ አገር ጎብኚዎች ሙሉ በሙሉ መቋረጡ ዘርፉን ጎድቶታል ነው ያሉት።

በዚህም ምክንያት ዘርፉን ዳግም ለማነቃቃት ሰፊ የቱሪዝም ፍሰት ይስተዋልባቸው በነበሩ የአማራና እና አፋር ክልሎች የዚህ አይነት መድረኮች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል።

በነዚህ ክልሎች በነበረው ጦርነት ምክንያት ሀገራት ዜጎቻቸው ወደነዚህ አከባቢዎች እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ከልክለው የነበረ ቢሆንም አሁን እየተሰራ ባለው ሥራ መሻሻሎች እየታዩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም በላሊበላ የውሃና መብራት አገልግሎት አለመኖሩ ትኩረት የሚፈልግ መሆኑ ተነስቷል።

በተጨማሪም በላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት ጋር በተያያዘ አየተነሱ ላሉ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሚልኪያስ አዱኛ