ተቋሙ በአማራ ክልል ከ1 ሺሕ 200 በላይ ሰዎች ፆታዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው ገለጸ

ሚያዝያ 11/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በአፋር እና አማራ ክልሎች ባደረገው ጥናት በአማራ ክልል ከ1 ሺሕ 200 በላይ ሰዎች ፆታዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው ገለጸ።

ተቋሙ በሁለቱ ከልሎች ያደረገውን የዳሰሳ ቁጥጥር አስመልክቶ መግለጫ እየሰጠ ይገኛል።

ተቋሙ በመግለጫው በአማራና አፋር ክልሎች አራት ቡድኖችን በማሰማራት ዳሰሳዊ ቁጥጥር ማድረጉን አስታውቆ አንደኛው ቡድን በአፋር ክልል ሀውሲና ፈንቲ ዞን በመዘዋወር ቁጥጥር  ያደረገ ሲሆን ሦስቱ ቡድኖች በአማራ ክልል 7 ዞኖች ቁጥጥር ማድረጋቸውን ገልጿል፡፡

በተደረገው ቁጥጥር አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና የአካባቢውን ነዋሪ እንዲሁም በመጠለያ ካምፕ የሚገኙ ነዋሪዎችን ለመመልከት መቻሉን አስታውቋል።

በአማራ ክልል 7 ዞኖች ባደረገው ቁጥጥር በጦርነቱ የተጎዱና የተፈናቀሉ ከ1 ሚሊየን 800 ሺሕ በላይ ሰዎች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የተቋሙ የሴቶች፣ ህፃናት፣ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች ዳይሬክተር ሰብለወርቅ ታሪኩ ተናግረዋል።

በተደረገው ጥናት ከ1 ሺሕ 200 በላይ ሰዎች የፆታ ጥቃት እንደደረሰባቸውም ገልፀዋል።

በአገልግሎት ሰጪ ተቋማትና በግል ተቋማት እንዲሁም በመሰረተ ልማቶች በተለይም በትምህርትና ጤና ተቋማት ዝርፍያና ውድመት መከናወኑ ነው የተገለፀው።

በመልሶ ማቋቋም ሂደት ውስጥም በሥነልቦናዊና ማኅበራዊ ድጋፍ መደረጉም ተመላክቷል።

ከማኅበረሰቡ ጋር በመመካከር ሂደት ውስጥ በትምህርትና ጤና ሴክተሩ ጠንካራ ሥራዎች መሰራቱም ተጠቁሟል።

የሚደረገው ድጋፍ ከስርጭት አንፃር የፍትሀዊነት ጥያቄ እንዳለም ነው የተገለፀው።

በአፋር ክልል የተፈናቀሉና ወደ ቀያቸው የተመለሱ እንዳሉ ሁሉ አሁንም የተፈናቀሉ ዜጎች እንዳሉ ተጠቁሟል።

በርካታ ውድመቶች በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ እንደደረሰም ተነግሯል፡፡

በክልሉ በአጠቃላይ ከ645 ሺሕ በላይ ዜጎች እንደተፈናቀሉም ነው የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ያስታወቀው።

የክልሉ መንግሥት ወረራውን ከመቋቋም ባለፈ የመልሶ ሟቋቋም ሂደቱ ላይ መስራቱን በኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የአስተዳደር በደል መከላከል ዳይሬክተር አዳነ በላይ ተናግረዋል።

በሱራፌል መንግሥቴ