ባለስልጣኑ አየር መንገዱን አስተማማኝ እና ተመራጭ የማድረግ ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ

ሚያዝያ 11/2014 (ዋልታ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ፣ መሰረተ- ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባለስልጣኑ አየር መንገዱን አስተማማኝ እና ተመራጭ የማድረግ ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህን ያለው በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ባደረገው የመስክ ምልከታ ወቅት ነው፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሸዊት ሻንካ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስተማማኝ እና ተመራጭ እንዲሆን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመው ተቋሙ ሀገሪቱ ላቀደችው እድገት ቀልጣፋ እና ውጤታማ ለመሆን ጠንካራ ተቆጣጣሪ ተቋም ሆኖ መቀጠል ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የአየር ትራንስፖርት አደጋ ስጋትን መቀነስ ላይ የተሰራውን ሥራ በጥንካሬ አንስተው በአንጻሩ ኅብረተሰቡ አስተማማኝ የአየር ትራንስፖርት እንዲያገኝ ከማስቻል ረገድ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ማሟላት ጊዜ የሚሰጠው እንዳልሆነ አስገንዝበዋል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግሥቴ የተቋሙን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ የሚገነቡ ኤርፖርቶች ዓለም ዐቀፍ ደረጃቸውን የሚጠብቁ መሆን ስላለባቸው የኤርፖርት ማስተር ፕላን ማዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሲቪል አየር ትራንስፖርትን መገንባት የሚያስችል አቅም እንዳላት አንስተው የአቪዬሽን ሴፍቲ ዓለም ዐቀፍ ስታንዳርዱን በሟሟላት የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናከር ሂደት ያለውን የአቪዬሽን ፖሊሲ አጽድቆ እና መዋቅር ማሻሻያ ሥራዎችን በፍጥነት አጠናቅቆ ወደ ሥራ ለመግባት በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የባለስልጣኑን የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውሮ በተመለከተበት ወቅት አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለው ራዳር ረጅም ጊዜ ያገለገለ በመሆኑ እና የሚያስከትለውን አደጋ ከግንዛቤ በማስገባት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ችግሩን በአጭር ጊዜ ሊፈታ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵን አየር ክልል በብቃት ለማስተዳደር እንዲሁም የአቪዬሽን ደኅንነት እና ሴኪዩሪቲ ቁጥጥርን አስተማማኝ እንዲሆን ከማድረግ አንጻር ግልጽ የሆነ እና ተጠያቂነት የሰፈነበት የአሰራር ሥርአት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ የጠቆመው ቋሚ ኮሚቴው ባለስልጣኑ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪን ከማስፋትም ሆነ ባለሃብቶችን በዘርፉ እንዲሳተፉ ከማድረግ ረገድ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ማሳሰቡን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!