በተደራጀ መልኩ ሀሰተኛ ማስረጃዎችን የሚሰሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በፎርጀሪ ሥራ የተሰማሩ ተጠርጣሪዎች

ሚያዝያ 13/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኹነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ በተደራጀ መልኩ በፎርጀሪ ሥራ የተሰማሩ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማደረጉን አስታወቀ።

በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ስሙ መሳለሚያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ክትትል ሲያደርግባቸው የነበሩ ፎርጅድ መሸኛ እና ሌሎች የፎርጀሪ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ አምስት ተጠርጣሪዎችን ከኤጀንሲው የክፍለ ከተማ ጽሕፈት ቤት እና ከየካ ፖሊስ መምሪያ ጋር በጋራ በመሆን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረግ ተችሏል።

ተጠርጣሪዎቹ የሚሰሯቸው ከክልል መሸኛ ፎርጀሪ ሰነዶች፣ የኹነት ማስረጃዎች፣ የክልል መታወቂያዎች፣ የትምህርት ማስረጃዎች፣ የፍርድ ቤት ዉሳኔዎች፣ የቤት ካርታዎችና ሌሎች ሰነዶች በኤግዚቢትነት ተይዘዋል።

ኅብረተሰቡ በወንጀል የሚያስጠይቅ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ ራሱን እንዲቆጥብ ኤጀንሲው አሳስቧል።

የኤጀንሲው ማስረጃዎች በቀላሉ ለፎርጀሪ የማይጋለጡ መሆኑን ኅብረተሰቡ በመገንዘብ በዚህ አይነት ድርጊት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ሲመለከት በነፃ የስልክ መስመር 7533 ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል።

ተጠርጣሪዎቹን በህግ ከለላ ሥራ ለማዋል እገዛ ላደረገው ለየካ ፖሊስ መምረያ ተቋሙ ምስጋናውን ማቅረቡን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW