ምዕመኑ የትንሳኤ በዓልን ያለው ለተቸገረ እያካፈለ እንዲያከብር ቤተ ክርስቲያኗ ጥሪ አቀረበች

ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

ሚያዝያ 13/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመኑ የትንሳኤ በዓልን ያለው ለተቸገረ እያካፈለ እንዲያከብር ጥሪ አቀረበች፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለእየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ፓትሪያርኩ በመልዕክታቸው በሀገር ውስጥ እንዲሁም ከሀገር ውጪ፣ በህመም ምክንያት በሆስፒታል፣ በጸበል እንዲሁም የሀገርን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ ለሚገኙ ምዕመናን እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

የሃይማኖት ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ የእየሱስ ክርስቶስን ይቅርባይነትና ሩህሩህነት በተከተለ ክትስቲያናዊ መርህ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።

የእየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ገዳማትና አድባራት በትልቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ይከበራልም ተብሏል።

ከትንሳኤ በዓል ቀደም ብለው የሚከበሩት የጸሎተ ሐሙስና የስቅለት በዓልም ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በተከተለ መንገድ እንደሚከናወን ተገልጿል።

በመስከረም ቸርነት

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW