“የትንሳዔ በዓል የላቀ ፍቅርን፣አክብሮትን ዝቅ በማለት የላቀ ከፍታ እንዳለ የምንረዳበት ነው” – አቶ እርስቱ ይርዳው   

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2014 (ዋልታ)– የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው  ለመላው ለክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ2014 ዓ.ም የትንሳዓ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት በዓሉ የሰላም፣የፍቅር እና የአብሮነት በዓል እንዲሆን  ተመኝተዋል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው የ2014 ዓ.ም  የትንሳኤን በዓል በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት  የትንሳኤ በአል እየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ ፍቅር እና አክብሮት የገለጸበት ነው ብለዋል።

ከትንሳዔ በዓል የላቀ ፍቅርን፣አክብሮትን ዝቅ በማለት የላቀ ከፍታ እንዳለ የምንረዳበት ነው ሲሉም ጠቁመዋል። በዓሉን ስናከብር በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ችግሮች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመርዳት እና በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው  በበዓላት ወቅት የመደጋገፍና የመረዳዳት የቆየ ባህላችንን ማጠናከር ይገባል ብለዋል። በተለይ አቅመ ደካማ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍ ፣በማይመች ሁኔታ ላይ ሆነው በዓልን የሚያሳልፉ ወገኖቻችንን አለንላችሁ ልንላቸው ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

ምንም እንኳን የውስጥ እና የውጭ ጠላቶቻችን ዛሬም ፈተናችንን ለማብዛት እና የብልጽግና ጉዟችንን ለማደናቀፍ ቢጥሩም ያጋጠሙንን ችግሮች ወደ መልካም እድል በመቀየር ወዳለምነው የእድገት ጉዞ እያቀናን ነው ብለዋል።

እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ አንድነታችንን እና ህብረታችንን ካጠናከርን እጅግ የገዘፈ የመሰለንን ችግር በቀላሉ መሻገር እንችላለን ለዚህ ደግሞ የመላው ህዝባችንን የላቀ ድጋፍ ይጠይቃል ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው እንዳሉት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከሰቱ ያሉ የሸቀጦች ዋጋ ንረትና በፀጥታ ችግሮች ምክንያት የተቀዛቀዘው ኢኮኖሚያችን ተዳምሮ የኑሮ ውድነት ህዝባችንን እየተፈታተነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

መንግስት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት መላው ህዝባችንን በማሳተፍ በከተማ እና በገጠር የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እያካሔደ ያለው ጥረት ሊጠናከር እንደሚገባም አብራርተዋል። በሁሉም ዘርፍ ምርታማነታችን ሲያድግ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥርልን ይሆናል ሲሉም በመልዕክታቸው አውስተዋል።

በሌላ በኩል ለኑሮ ውድነቱ መንስኤ የሆኑ ሰው ሰራሽ  ችግሮችን መፈተሽ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በንግድ ስርዓቱ ላይ የሚስተዋለውን ህገ ወጥነት በመከላከል ረገድ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ሊሆን ይገባል ሲሉም አብራርተዋል።