የላስታ ወረዳ ነዋሪዎች ለክፍለጦሩ የዕርድ እንስሳት ድጋፍ አደረጉ

ሚያዝያ 16/2014 (ዋልታ) የላስታ ወረዳ ነዋሪዎች የፋሲካን በዓል ምክንያት በማድረግ በደቡብ ዕዝ ስር ለሚገኝ ክፍለጦር የዕርድ እንስሳት ድጋፍ አድርገዋል።

ኅብረተሰቡን በመወከል ድጋፉን ያስከረቡት ወንድምነው ወዳጅ “የኢትዮጵያን ሠላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ በሰላም እንድንኖር ላደረገው ሰራዊት ድጋፍ ስናደርግ በታላቅ ደስታ ነው” ብለዋል።

ሌላው የወረዳዋ ነዋሪ ቢራራ ያረጋል መከላከያ ሠራዊት ለሀገሪቱ እየከፈለ ያለውን ጀግንነት አድንቀው የወረዳው ሕዝብ ለሠራዊቱ ድጋፍ ያደረገው ያለውን አክብሮትና ምስጋና ለመግለፅ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለከፈለ ሠራዊት ድጋፍ ማድረግ ቢያንስበት እንጂ አይበዛበትም ሲሉም የወረዳው ማኅበረሰብ ተወካዮች መናገራቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የዕርድ እንስሳት ድጋፉን የተረከቡት የክፍለ ጦሩ ዋና አዛዥ ብ/ጄነራል ተክሉ ሁሪሳ በበኩላቸው “በጦርነት በተጎዳ አካባቢ ሆናችሁ ይህንን ድጋፍ በማድረጋችሁ እጅግ ኮርተንባችኋል፣ ኅብረተሰቡ በዘመቻ ወቅትም ደጀንነቱን በተግባር ያስመሰከረ እና የምንኮራበት ነው” ብለዋል።