አቶ አህመድ ሽዴ እና ሳማንታ ፓወር ተወያዩ

ሚያዝያ 18/2014 (ዋልታ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በአሜሪካና ኢትዮጵያ የልማት ትብብር፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙርያ ከዩኤስኤይድ ሃላፊ ሳማንታ ፓወር ጋር ተወያይተዋል።

ውይይታቸው ያተኮረው በኢትዮጵያ በግጭቶች ምክንያት ስለተከሰቱ ችግሮች፣ በቀጠናው ስለተጋረጠው ረሃብና ወቅታዊው የአለም ሁኔታ ስላስከተለው የምግብ ደህንነት ስጋት ነው።

በዚህ ወቅት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ሉዓላዊነትን፣ የህዝብን ጥቅምና ፍላጎት ባስጠበቀ መልኩ መንግስት የሚያከናውነውን የድጋፍና ሰላም የማስከበር እንዲሁም አካታች የፖለቲካ ስርኣት የመገንባት ተግባራት አብራርተዋል።

በተጨማሪም በአፋር፣ አማራና ትግራይ ክልሎች ሰብአዊ ድጋፎችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ ወቅታዊ ትክክለኛ ሁኔታው ምን እንደሚመስል ያስረዱት ሚኒስትሩ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ከሌሎች አጋር አከላት ጋር እየተከናወኑ ስለሚገኙ ጉዳዮች ግንዛቤ ሰጥተዋል።

ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የአሜሪካ እርዳታ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) በቀጠናው የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ ስለሚቀጥልበት ሁኔታ በውይይቱ ተነስቷል።