ቢሮው ከእቅዱ በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ

ሚያዝያ 18/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የዋጋ ንረትና ኑሮ ውድነት የፈጠረውን ጫና በመቋቋም በኅብረተሰቡ ላይ ጫና ሳይፈጠር ከእቅዱ በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አስታወቀ።

ቢሮው የ2014 ዓ.ም ባቀረበው የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት መሠረት ከ43 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ነው የገለፀው።

የቢሮው ኃላፊ ሙሉጌታ ተፈራ በዘጠኝ ወራት ለመሰብሰብ ታቅዶ የነበረው 37 ቢሊዮን ብር ቢሆንም ከታቀደው በላይ ገቢ ሊገኝ ችሏል ብለዋል።

ቢሮው በበጀት ዓመቱ በአምስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አትኩሮ የነበረ ሲሆን የተቋሙን አቅም ማጎልበት፣ የአገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን፣ ከሌሎች ተቋማት ጋር መተባበር፣ የህግ ተገዢነትን ማጠናከር እና ገቢን ማሳደግ የሚሉት ናቸው።

ከ400 ሺሕ በላይ ደንበኞች ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዮች ቢሮ ተቋሙን የበለጠ በማዘመን የተገልጋዩን ፍላጎት ለሟሟላት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በቢሮው ስም ወንጀል የሚሰሩ አካላት፣ የሥነ-ምግባር ችግር ባለባቸው ባለሙያዎችና ገቢን በመሰወር ወንጀል ላይ በተሰማሩ ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ሕግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

በሚልኪያስ አዱኛ