አገራዊ ምክክሩ በአራት ምዕራፎች ተከፋፍሎ እየተሰራ ነው

ሚያዝያ 18/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሥራዎችን በአራት ምዕራፎች ከፋፍሎ እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።
ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸውን በቀጣይ ስለሚያከናውናቸው ተግባራት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና ለምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች እያቀረበ ይገኛል።
የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ መስፍን አርአያ (ፕ/ር) ኮሚሽኑ እስካሁን የሠራቸውን ተግባራትና በቀጣይ ስለሚያከናውናቸው ተግባራት ሪፖርት አቅርበዋል።
በዚህም አገራዊ ምክክሩ በአራት ምዕራፎች ከፋፍሎ ሥራ መጀመሩን ነው የገለጹት።
እነዚህም የቅድመ ዝግጅት፣ የዝግጅት፣ የምክክርና ክንውን ሂደትና የምክክር ውጤቶች መተግበሪያ ምዕራፎች መሆናቸውን ዘርዝረዋል።
በእነዚህ ምዕራፎች የተከናወኑትንና ወደ ፊትም የሚሰሩትን ሥራዎችም አስረድተዋል።
በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና ከፍተኛ አመራሮች አስተያየትና ቀጣይ አቅጣጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።