በሃይማኖት ሽፋን ግጭት የሚፈጥሩ አካላትን መታገል እንደሚገባ የጎንደር የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ

ሚያዝያ 19/2014 (ዋልታ) በጎንደር ከተማ በትላንትናው ዕለት በሃይማኖት ሽፋን የተፈጠረው ችግር የሁለቱንም ሃይማኖት አማኞችን የማይወክል ነው ሲል የጎንደር ከተማ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ድርጊቱን አውግዟል፡፡

ጉባኤው የተፈጠረው ግጭት በሌሎች አካላት የተቀነባበረ ሴራ እንደሆነና ጎንደርን ለማወክና ለማበጣበጥ የታሰበ እንደሆነ ነው የገለጸው፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ አባ ዮሴፍ ደስታ እንደተናገሩት በጎንደር ከተማ የተከሰተው ግጭት ሰላምን በማይሹ፣ ለሰላም ዋጋ በማይሰጡ ሰዎች የተፈጠረ ችግር ነው፤ ይህንን ችግር ደግሞ ለዘመናት በአብሮነት የሚኖሩ የሁለቱ ሃይማቶች በጋራ መታገል እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ቤተክርስቲያኒቱ ለሰላም ትሠራለች ያሉት አባ ዮሴፍ ደስታ ችግሩ በውይይትና በመነጋገር እንዲፈታም ይሠራል ብለዋል፡፡

የጎንደር ወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት አገልጋይ አማን ሷሊህ በበኩላቸው ግጭት ለማስነሳት የሞከሩ አካላት በእምነት ሽፋን ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳን ለማራመድ የሚሹ ናቸው ብለዋል።

የሁለቱም ሃይማኖቶች አስተምህሮ ይህንን አይፈቅድም ሲሉ ማውገዛቸውን አሚኮ ነው የዘገበው።

ጉባኤው ለሰው ሕይዎት መጥፋትና ለንብረት መውደም ምክንያት የሆኑ ግለሰቦችን መንግሥት በፍጥነት ለሕግ ማቅረብ ይገባዋልም ነው ያሉት፡፡

አሁን ላይ በከተማዋ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳለ የገለጹት የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላቱ በቀጣይ ሁለቱም ሃይማኖቶች ለሰላም ትኩረት በመስጠት የጎንደር የቀደመ አብሮ የመኖርና የመቻቻል ባሕልን ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡