የኢትዮጵያ ምሁራንና የሲቪክ ተቋማት አሚኔስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዎች ያወጡትን ሪፖርት አወገዙ

ሚያዚያ 19/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ የሲቪክ ተቋማት እና ምሁራን አሚኔስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዎች ከወልቃይት ጋር በተያያዘ ያወጡትን ሪፖርት አውግዘዋል፡፡

ሁለቱ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ይፋ ባደረጉት ሪፖርት የኢትዮጵያን መንግስት፣ የአማራ ክልላዊ መንግስትን፣ የአማራ ሚሊሻ እና ፋኖን በሰብዓዊ መብት ጥሰት መወንጀሉ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ምሁራን እና የሲቪክ ተቋማት በዚህ ጥምር ሪፖርት ዙሪያ ባወጡት የአጸፋ ምላሽ ጠንከር ያሉ ትችቶችን ያቀረቡ ሲሆን፣ ሪፖርቱ ለአንድ ወገን ያደላ፣ ተጨባችነት የሌለው እና ፍጹም ተአማኒነት የጎደለው ነው ብለዋል፡፡

ምሁራኑና የሲቪክ ተቋማቱ መሪዎች ለሁለቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሪፖርት በሰጡት ምላሽ ወልቃይትን በስያሜው ከመጥራት ይልቅ ትሕነግ የሚጠቀምበትን “ምዕራብ ትግራይ” እያለ መጥራቱ፣ ለአንድ ወገን ያደላ በመሆኑ፣ መረጃ የተሰበሰበበት አግባብ የተሳሳተ መሆኑ እና ሪፖርቱ የቀረበበት ጊዜ ሪፖርቱን ተአማኒነት እንደሚጎድለው አመላካች ነጥቦች ናቸው ብለዋል፡፡

ሁለቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን የሚሉ ተቋማት አምባገነኑ የትሕነግ ቡድን ባለፉት በርካታ አመታት በወልቃይት ላይ የፈጸማቸውን በደሎች እና ግፎች አድበስብሶ ለማለፍ መሞከራቸውንም ተችቷል፡፡

ይሁን እንጂ ለበርካታ አመታት ዘግናኝ ተግባራትን በሰዎች ላይ የፈጸመው የትሕነግ አመራሮችን በሰብዓዊ መብት ጥሰት መክሰስ ያለፈለገው ይህ ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግስትን ጨምሮ የአማራ ክልል መንግስትን፣ ሚሊሻና ፋኖን በዚህ ተግባር መወንጀሉ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ከትግራይ ክልል ተፈናቅለው በሱዳን የመጠለያ ጣቢያዎች ከተጠለሉ አካላት ብቻ የተገኙ መረጃዎችን ለጥናቱ በዋና ግብአትነት መጠቀማቸው በራሱ እውነታውን ለማድበስበስ እየተደረገ ያለውን ጥረት አመላካች መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በኢትዮጵያ ምሁራን እና የሲቪክ ማህበራት ለሁለቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሪፖርት ያዘጋጁትን ምላሽ 193 ምሁራን እና 37 የሲቪክ ተቋማት ኃላፊዎች መፈረማቸውን ዋልታ ያገኘው ሰነድ ያመለክታል፡፡

በነስረዲን ኑሩ