በ9 ወራት ከ351 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

ሚያዝያ 19/2014 (ዋልታ) በዘጠኝ ወራት ውስጥ በሀገሪቱ የታክስ ተቋማት አማካኝነት በጥቅሉ ከ351 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ በፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር እና ጉምሩክ ኮሚሽን፣ በከተማ መስተዳደሮች እንዲሁም በክልሎች የታክስ ተቋማት አማካኝነት ለመሰብሰብ ከታቀደው 372 ነጥብ 121 ቢሊዮን ብር የ351 ነጥብ 949 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም የ94 ነጥብ 58 በመቶ አፈጻጸም እንደተመዘገበና ከባለፈው የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ59 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወይንም የ17 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ገቢ ውስጥ በፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር እና በጉምሩክ ኮሚሽን አማካኝነት የተሰበሰበው የዘጠኝ ወራት ገቢ 248 ነጥብ 6 ቢሊዮን መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡
ሚኒስትሩ ብዙ የገቢ ዘርፍ ተቋማት በተለያዩ ችግሮች ውስጥ በነበሩበት እና ባሉበት እንዲሁም ኢኮኖሚው በተቀዛቀዘበት ወቅት የተገኘው አፈጸጸም ጥሩ የሚባል መሆኑን ጠቅሰው ይህ እንዲሆን ላስቻሉት አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የ2014 በጀት ዓመት የመልካም የሥራ ግንኙነት መድረክ በፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር እና ጉምሩክ ኮሚሽን፣ በከተማ መስተዳደሮች እንዲሁም በክልሎች የታክስ ተቋማት መካከል እየተካሄደ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡
ለፈጣን መረጃዎች፦
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!