ኢትዮጵያ ማስቀጠል የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን በመገንዘብ እንተጋገዝ – ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር ኢድሪስ

ሚያዝያ 19/2014 (ዋልታ) ሙስሊም ክርስትያኑ ተከባብሮና ተመካክሮ የኖረባትን ኢትዮጵያ ማስቀጠል የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን በመገንዘብ እንተጋገዝ ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር ኢድሪስ ጥሪ አቀረቡ።
“ከኢድ እስከ ኢድ” ወደ ሀገር ቤት መርኃ ግብር በወዳጅነት አደባባይ እየተካሄደ ይገኛል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪን ተከትሎ ወደ ሀገራቸው የገቡ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዒድን በእናት ሀገራቸው ለማክበር ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል።
የዲያስፖራን አቅም በመጠቀም ሀገራት ኢኮኖሚያቸውን ሲያሳድጉና ሀገር ሲያለሙ መመልከት የተለመደ ሲሆን “ከኢድ እስከ ኢድ” ወደ ሀገር ቤት ጥሪ የዲያስፖራውን ተሳትፎ በማጎልበት ሀገርን መገንባት ብሎም በልማት ሥራዎች ላይ ተሳታፊ ማድረግ እንደሚያስችል ይታመንበታል።
በመርኃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር ኢድሪስ ቅዱስ ቁርዓንም ተባብረህ ሥራ ይላልና ከሀገር ውስጥም ከውጪም ያሉ ኢትዮጵያዊያን መሰብሰብ እርስ በእርስ ያገናኛል፤ ያግባባል፤ ሰላምም ያሰፍናል ሲሉ ገልፀዋል።
ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሀገር ቤት መርኃ ግብር ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በሃኒ አበበ