የሁሉም ቤተ እምነት ተከታዮች መረጋጋትና ሰላም ማስፈን አለባቸው ተባለ

ሚያዝያ 19/2014 (ዋልታ) በጎንደር ከተማ በሃይማኖት ሽፋን ለተከሰተው የፀጥታ ችግር መንግሥት ጉዳዩን አጣርቶ ለወንጀለኞች ተገቢውን ፍርድ እስከሚሰጥ የሁሉም እምነት ተከታዮች እንደየሃይማኖቶች አስተምሕሮ መረጋጋትና ሰላምን ማስፈን እንዳለባቸው የክልሉ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ገለጸ፡፡
የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በትናንትናው ዕለት በጎንደር ከተማ በሃይማኖት ሽፋን የተከሰተውን የፀጥታ ችግር በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።
የጉባዔው ቦርድ ተወካይ ሰብሳቢ መላከ ብርሃን ፍስሃ ጥላሁን ድርጊቱ ፈጽሞ የሁለቱን የእምነት ተከታዮች የማይወክልና ሊወገዝ የሚገባው መሆኑን የተናገሩ ሲሆን በተፈጠረው ክስተት ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ጉዳዩን አጣርቶ ለወንጀለኞች ተገቢውን ፍርድ እስከሚሰጥ የሁሉም እምነት ተከታዮች እንደየሃይማኖቶች አስተምሕሮ መረጋጋትና ሰላሙን ማስፈን አለባቸውም ሲሉም ገልጸዋል።
የክልሉ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ምክትል ተወካይ ቦርድ ሰብሳቢ ሃጅ የሱፍ ማሩ “በጎንደር ከተማ የተከሰተው ግጭት ለዘመናት አብረው የኖሩትን የሁለቱንም እምነት ተከታይ ሕዝቦች ክብርና መተሳሰብ የማይወክል ነው፤ በተለይም በታላቁ የረመዳን ወቅት ክርስቲያኑ በሙስሊሙ የኢፍጣር ዝግጅት ላይ እየተገኘ ከጎናችሁ ነን በሚልበት ወቅት ይህ መሆኑ የሕዝቦችን የቆየ አብሮነት የማይወክል ለመሆኑ ማሳያ ነው” ብለዋል።
በተፈጠረው ክስተት ማዘናቸውን የገለጹት ሃጅ የሱፍ ሁሉም በሰከነ መልኩ ለሰላም የራሱን ሚና መወጣት አለበት ነው ያሉት።
የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የቦርድ ጸሃፊ መጋቢ ገብሬ አሰፋ በበኩላቸው በከተማው ውስጥ የገባውን የሁከት ክፉ ሴራ አክሽፎ አብሮ ለመኖር አባቶችና ወጣቶች በሰከነ መልኩ መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የጉባኤው የቦርድ አባል አባ ስንታየሁ ገላው በበኩላቸው “አሁን ላይ እንደ ክልልና እንደ ሀገር መሥራት ያለብን አጀንዳዎች ላይ ማተኮር እንጅ ለአብሮነታችን የማይጠቅም ተግባር ላይ መሳተፍ ወደ ጥፋት እንጅ ወደ ልማት ስለማይወስደን ፈጽሞ መተው ያስፈልጋል” ብለዋል።
መንግሥት አጥፊዎችን ለይቶ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ማሳሰባቸውን አሚኮ ነው የዘገበው፡፡
“ወጣቶች የሁለቱንም ሃይማኖት ተከታዮች ከሚያሳዝን ተግባር ራሳቸውን ቆጥበው ለሕዝብና ለሀገር ሰላም መቆም አለባቸው” ነው ያሉት።