ጉባኤው በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ጠብ አጫሪ መልዕክቶችን ማውገዝ እንደሚገባ አሳሰበ

ሚያዝያ 20/2014 (ዋልታ) በጎንደር ከተማ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ጠብ አጫሪ መልዕክቶችን ማውገዝ እንደሚገባ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳሰበ፡፡

የኢትዮጵያ  የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በጎንደር ከተማ  የተከሰተውን የፀጥታ ችግር በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የጉባኤው ጠቅላይ  ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በሰጡት መግለጫ ለዘመናት ተከባብረው በኖሩ ሕዝቦች ላይ የተፈጠረውን ግጭት አውግዘዋል፡፡

የሁሉም ቤተ እምነት ተከታዮች እንደ ሃይማኖቶች አስተምሕሮ መረጋጋትና ሰላምን ማስፈን እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡

ድርጊቱ ፈጽሞ የሁለቱን የእምነት ተከታዮች የማይወክልና ሊወገዝ የሚገባ ነው ተብሏል፡፡

መንግሥትም ጉዳዩን አጣርቶ ለወንጀለኞች ተገቢውን ፍርድ መስጠት እንዳለበት ተነግሯል፡፡

በታሪካዊቷ ከተማ የተከሰተው ግጭት ለዘመናት አብረው የኖሩትን የሁለቱንም እምነት ተከታይ ሕዝቦች ክብርና መተሳሰብ የማይወክል መሆኑን ሁሉም ኅብረተሰብ ሊረዳው ይገባልም ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በተፈጠረው ክስተት ማዘኑን በመግለፅ ሁሉም የእምነት  አባቶች ለሰላም ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

በአመለወርቅ መኳንንት