ጠ/ሚ ዐቢይ አጥፊውን አውግዘን ከተጠቂው ጋር እንቆማለን እንጂ ጥፋቱን በሌላ ጥፋት ለማባባስ መሞከር የለብንም አሉ

ሚያዝያ 20/2014 (ዋልታ) አጥፊውን አውግዘን ከተጠቂው ጋር እንቆማለን እንጂ ጥፋቱን በሌላ ጥፋት ለማባባስ መሞከር የለብንም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
እንደ ሕዝብ ልዩነቶቻችንን አምነን ተቀብለን በብዙ ትውልዶች ዕድሜ በኁባሬ ተሣሥረን ኖረናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋራ ስፌታችን ውስጥ መቻቻል አንዱ አስፈላጊ ሰበዝ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ እንደ አንድ ሕዝብ የሀገራችንን መጥፋት የሚፈልጉ ሁሉ የጥፋት ዕቅዳቸው ወኪል አድርገው እንዲወስዱን ልንፈቅድ አይገባም ብለዋል፡፡
በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ውስጥ እንዲሆን የምንፈቅድለት ክፋት ከእርስ በርስ ተዛምዷችን ጋር ካለው ቅርበት ይልቅ ለሌሎች የጥፋት ወኪሎች መጠቀሚያ የሚሆን ነው ሲሉም በመልዕክታቸው አክለዋል።
በማኅበረሰባችን ውስጥ የአስተዋዮችን ልቡና እንፈልግ እና ልዩነቶችን ከማጉላት ይልቅ ለማቀራረብ እንሥራ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የምንጋራው ሰብአዊነት ይህንን እንድናደርግ ያስገድደናል ነው ያሉት።
ማንንም ለማጥፋት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግ ጥቃት በሁላችን ላይ የሚደረግ ነው ብለዋል።
አጥፊውን አውግዘን ከተጠቂው ጋር እንቆማለን እንጂ ጥፋቱን በሌላ ጥፋት ለማባባስ መሞከር የለብንም ሲሉም አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኢትዮጵያ ሰላም እንጂ ከኢትዮጵያ ሑከት ማናችንም አናተርፍም ብለዋል።