አፍሪካ ያሏትን ጥበብና ባህል ሰላምን ለማረጋገጥና መረጋጋትን ለማስፈን ልትጠቀም እንደሚገባ ተገለጸ

ሚያዝያ 22/2014 (ዋልታ) አፍሪካ ያሏትን ጥበብና ባህል ሰላምን ለማረጋገጥና መረጋጋትን ለማስፈን ልትጠቀም ይገባል ሲሉ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በቀጣናውና በአኅጉሪቱ የሚታዩትን አለመረጋጋቶች ለመከላከል አፍሪካዊ የግጭት አፈታት ጥበቦችን መጠቀምና ለዚህም የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት በአዲስ አበባ ሲያደርግ በነበረው የውይይት ማጠቃላያ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የመከላከያ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የፀጥታ አካል የሆነው የምስራቅ አፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይል የሀገር ሽማግሌዎች መማክርትም አፍሪካዊያን ችግራችንን በራሳችን መንገድ ለመፍታት ያስቀመጥነውን ራዕይ ለማሳካት አጋዥ ነው ብለዋል።

የሽማግሌዎች ያላቸውን ልምድና ዕውቀት ተጠቅመው ከመሪዎችና ከሚመለከታቸው ጋር በቅርበት እንዲሰሩና መማክርቱ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ እንደማይለያቸውም አረጋግጠዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የተጠባባቂ ኃይል ዋና ዳይሬክተር ብ/ጄ ጌታቸው ሽፈራው የወርክሾፑ ዓላማ ከአባል ሀገራት የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎችን ለማቀራረብና የቀጣናውን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል ምክረ ሀሳቦችን ለማቅረብ መሆኑን ገልፀው ቆይታቸው ውጤታማ እንደነበር ተናግረዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የሽማግሌዎች መማክርት ሰብሳቢ የቀድሞው የብሩንዲ ፕሬዝዳንት ዶሚቲን ንዳይዜ መማክርቱ ያሏቸውን ልምድና ዕውቀት ተጠቅመው በትክክለኛ መረጃ ላይ በመመስረት ግጭቶች ሳይፈጠሩ ለመከላከል በሙሉ አቅማቸው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የተጠባባቂ ኃይል የሽማግሌዎች መማክርት ለረጅም ዘመን በአመራርነት ልምድና ዕውቀቱ ባላቸው አምባሳደሮችና ከፍተኛ የጦር አመራሮች የተዋቀረ መሆኑን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!