ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሃይማኖት ልዩነት አጥር ሆኖብን አያውቅም አሉ

ሚያዝያ 22/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ትላንት በመዲናዋ የተካሄደው ታላቅ የጎዳና ላይ ኢፍጣር በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
ከንቲባዋ በምስጋና መልዕክታቸው “የሃይማኖት ልዩነት አጥር ሆኖብን አያውቅም” ብለዋል።
“እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደ ድርና ማግ ተዋኅደን የኖርን፣ በአንድነት የተዋደቅን፣ ክፉና ደጉን የተጋራን፣ በተባበረው ክንዳችን ሀገራችንን ያፀናን፤ ልዩነትን በጥበብና በስክነት ይዘን መኖር የምናውቅበት ድንቅ ሕዝቦች ነን” ያሉት ከንቲባዋ ሃይማኖቶቻችን የበጎ ነገሮች ሁሉ መፍለቂያ ናቸው፤ የቅንነት፣ የትህትና፣ የመከባበርና በአብሮነት የመኖር እና የሰላም ባለቤቶች ናቸው” ብለዋል በመልዕክታቸው።
እነዚህ ውብ እሴቶቻችን በኢትዮጵያዊነት እሴቶች ሲታጀቡ ደግሞ መድመቂያ ፈርጦቻችን ናቸው ያሉት ከንቲባዋ፥ “አብሮነታችንን አጥብቀን የምንፈልግ ህዝቦችም ነን። ይህ ድንቅ እሴታችን እንዳይደበዝዝ ዛሬ ላይ ሁላችንን ታላቅ ሃላፊነት አለብን” ነው ያሉት።
“ስለዚህ፣ ወገኖቼ ፈተናዎችና ፈታኞችም በጊዜና በሁኔታ ይመጣሉ ይሄዳሉ፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ግን ፀንተው ዘመናትን ይሻገራሉ፡፡ እናም ይህንን ወቅት ቆም ብለን እናስብ። ከስሜት ወጥተን በተረጋጋ መንፈስ ግራና ቀኝ ተመልክተን እንሻገር። ለአንድነታችንና ለሰላማችን ይበልጥ እንተባበር” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
“የሚበልጥብን ፍቅራችን ነው፤ የሚያምርብን አንድነታችን ነው፤ የሚሰምርልን በጋራ መኖራችን ነው፡፡ ዛሬ ላይ ነገ የሚቆጨንን ተግባር ላለማድረግ በጋራ እንቁም” ብለዋል ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክታቸው።
ትላንት በአዲስ አበባ የተካሄደው ታላቅ የጎዳና ላይ ኢፍጣር በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት በሙሉ በከተማ አስተዳደሩና በነዋሪው ስም የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።