ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳው ለኢድ- አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ሚያዝያ 23/2014 (ዋልታ) የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳው ለ1443ኛው ለኢድ- አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ሕዝበ ሙስሊሙ በቅዱሱ የረመዳን ወር ለአገራችን ሰላም እና ለሕዝቦች አንድነት በጾምና በጸሎት ሌት ተቀን ሲተጋ ቆይቷል።

መረዳዳት እና መደጋገፍ ጎልቶ በሚታይበት በዚህ የጾም ወቅት የታየው መልካም እሴት በቀሪ ጊዜያትም ሊጠናከር ይገባል።

የኢድ አል ፈጥር በዓል የእዝነትና የርህራሄ፣ የመተሳሰብ፣ ያለው ለሌው በማካፈል በአብሮነት የሚያሳልፈው እና ማህበራዊ ግንኙነትን የበለጠ የሚያጠናከርበት በመሆኑ በተለይ በዚህ የችግር ወቅት መላው ህዝበ ሙስሊም በዓሉን በመደጋገፍ እና በመረዳዳት ሊያሳልፈው ይገባል።

በአሁኑ ሰዓት በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ችግሮች የሌሎች ሰዎችን ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመደገፍ ይጠበቅብናል።

ለዚህም ከእምነቱ ድንቅ እሴቶች አንዱ የሆነውንና አቅሙ ያለው ሙስሊም በነፍስ ወክፍ  የሚያወጣውን “የዘካተል ፍጥር” የእህል ስጦታ በማስተባበር በብዙ መልኩ ችግር ውስጥ ላሉ ሰዎች በማበርከት የወገን አለኝታነቱን እንዲወጣ እጠይቃለሁ።

በሌላ በኩልም አሁን ላይ አገራችን እንዳትረጋጋ የሚሹ ሀይሎች አንዴ የብሔር ገጽታ በሌላ ጊዜ ደግሞ የሀይማኖት ሽፋን በመስጠት ህብረተሰቡን እያሸበሩ ይገኛሉ።

ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እያስተናገደች የገጠሟትን ፈተናዎች ደግሞ በህዝቦቿ ብርቱ ጥረት በጽናት እየተሻገረች ላለችው ሀገራችን የሰላም እጦት ሲጨመር እድገታችንን ወደ ኋላ መጎተቱ አይቀርም።

በዚህ ደግሞ ተጎጂ የምንሆነው ሁላችንም ነን እንጂ ጥቂቶች ብቻ አይደሉም።

ጎረቤት ሰላም ካልሆነ፣ እኛም  ሰላም አንሆንምና  ሰላም የሰፈነባትና የበለፀገች አገር ለመጪው ትውልድ ማስረከብ የሁሉም ኀላፊነት ሊሆን ይገባል።

በተለይም ደግሞ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተምሳሌት ሆነው ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ አገር አንድነት ሊያስተምሩና ሊመክሩ ይገባል።

ሰሞኑን ለዘመናት ተቻችለው እና ተከባብረው በኖሩ የእስልምና እና የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ቅራኔ እንዲፈጠር የሚሹ አካላት የነሱን ጉዳይ አስፈጻሚዎች በመጠቀም በሀይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ምክንያት ሆነዋል።

በክልላችንም ሆነ በሀገራችን እየተስተዋለ ያለው ጽንፈኝነት ከእምነቶች አስተምህሮት ባፈነገጠ መልኩ የግል ፍላጎት እና የፖለቲካ ትርፍ ማካበት በሚፈልጉ አካላት የሚፈጸም እንደሆነ እሙን ነው።

ሕዝበ ሙስሊሙም ሆነ የሌላው እምነት ተከታይ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የጽንፈኝነት እንቅስቃሴዎችን የከፋ አደጋና ጉዳት እንዳያደርስ ካላከሸፈ የመጀመሪያ ተጎጂው ራሱ በመሆኑ ከወዲሁ አምርሮ በተደራጀ መልኩ መታገል ይኖርበታል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም የሰላም እጦት ያጋጠማቸው አካባቢዎች በዓልን ማክበር ከባድ ሆኖባቸው ይገኛሉ። በዓሉን ስናከብር እነዚህን ወገኖች እያሰብን መሆን እንዳለበት ለማሳሰብ እወዳለሁ።

በቀጣይም ቢሆን መላው የክልላችን ሕዝብ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ እንዲሁም ለዘመናት የገነባነውን የሰላም፣የመቻቻል፣የአብሮነት፣ የመከባበር እና የመደጋገፍ እሴት በማጠናከር ሀገራዊ የለውጥ ጉዞውን እንዲያሳካ ጥሪየን አቀርባለሁ።

በመጨረሻም በዓሉ የሰላም፣የፍቅር፣የአብሮነት እና የመተሳሰብ እንዲሆን መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ።