ታላቁን የኢድ ሰላት ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቋል

ሚያዝያ 23/2014 (ዋልታ) ታላቁን የኢድ ሰላት በኢትዮጵያ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን፣ የጎረቤት አገራት የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም በአዲስ አበባና አካባቢዋ የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት የታላቁ ኢድ ሰላት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ከኢድ እስከ ኢድ ብሔራዊ ኮሚቴ ሴክሬታሪያትና የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በጋራ ባደረጉት ስብሰባ አስታውቀዋል፡፡

በወቅቱም የዘንድሮው የዒድ ሰላት ከዚህ በፊት ከነበሩት በተሻለ ቅንጅት ተሰርቶ ለአገር ገፅታ ግንባታ ከፍተኛ ሚና እንዲጫወት የሁሉንም አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል፡፡

ጥሪ የተደረገላቸው የጎረቤት ሀገራት አቻ ተቋማት ተወካዮችም በክብር እንግድነት ለመገኘት ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም በበዓሉ ላይ ለመታደም አስቀድመው መግባት መጀመራቸውም ተጠቁሟል፡፡

የዚህ ዓመት የኢድ ሰላት ስግደት ከከተማው ሁሉም አካባቢዎች በመሰባሰብ በጋራ ለመስገድ በሚያስችል መልኩ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚካሄድ መሆኑን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ኮሚቴው ጥሪውን አክብረው በዓሉ ላይ ለመታደም ለመጡ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች መልካም የኢድ አልፈጥር በዓል እንዲሆን ተመኝቷል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW