“ታላቁ የኢድ ሰላት በኢትዮጵያ ” በአዲስ አበባ ስታዲየም እየተካሄደ ነው

ሚያዝያ 24/2014 (ዋልታ) “ታላቁ የኢድ ሰላት በኢትዮጵያ” የእስልምና እምነት አባቶች፣ የእምነቱ ተከታዮች ፣ የጎረቤት አገራት የእስልምና ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት በአዲስ አበባ ስታዲየም በመካሄድ ላይ ነው።
የእምነቱ ተከታዮች ታላቁን የረመዳን ወር በዱኣ፣ በሰላት፣ በፆም እና የተለያዩ በጎ ተግባራትን በማከናወን ማሳለፋቸው አይዘነጋም።
የሕዝበ ሙስሊሙ የፆም መገባደጃ ምልክት የሆነችው ጨረቃ በመታየቷ ኢድ አልፈጥር በዛሬው ዕለት በተለያዩ መርኃ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።
ከመርኃ ግብሮቹ መካከል የሆነው “ታላቅ የኢድ ስግደት” በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
“ከኢድ እስከ ኢድ” ጥሪ ጋር በተያያዘ ከተዘጋጁ መርኃ ግብሮች መካከል አንዱ በሆነው “ታላቁ የኢድ ሰላት”
በኢትዮጵያ ላይ ለመታደምም የጎረቤት አገራት የእስልምና ተቋማት ተወካዮችም በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ፤ ሕዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወር ያዳበራቸውን መልካም ስራዎች ከረመዳን ውጪ ባሉት ወራትም የተራቡትን በማብላት፣ የታረዙትን በማልበስና የተቸገሩትን በመርዳት እንዲሁም የማዕድ ማጋራቱን ስራ በቀጣይነት በመፈፀም ከፈጣሪው የሚያገኘውን ምንዳ ከፍ ማድረግ ይኖርበታል ማለታቸው ይታወሳል።
በደምሰው በነበሩ