አምራች ኢንዱስትሪዎች የኃይል አቅርቦት ችግር እንዳይገጥማቸው እገዛ እየተደረገ ነው

አምራች ኢንዱስትሪዎች

ሚያዝያ 25/2014 (ዋልታ) የአምራች ኢንዱስትሪ ደንበኞች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ የኃይል አቅርቦት ችግር እንዳይገጥማቸው እገዛ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

በአገልግሎቱ የኢንዱስትሪ ደንበኞች የኃይል አቅርቦት ማስተባበሪያ ኃላፊ ነብዩ በየነ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቶችን፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን፣ ከውጭ ሀገር የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ወስጥ ለመተካት የሚሰሩ አምራች ድርጅቶችን፣ የአበባ ልማቶችን እንዲሁም የብረታ ብረት፣ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት አቅራቢ ድርጅቶችን በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ለማገዝ እየተሰራ  ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም ከኢንቨስተሮች ወደ ማስተባበሪያ ክፍሉ የሚመጡ የአዲስ ኃይል ጥያቄ፣ የኃይል መቆራረጥ፣ የኃይል ማሻሻያ እና ከቢል ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ተቀብሎ እንዳስፈላጊነቱም ጥናት በማድረግ ለጥያቄዎቻቸው መፍትሄ እንደሚሰጥም አመላክተዋል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት አዲስ ኃይልና ተጨማሪ ኃይል ለሚፈልጉ ኢንዱስትሪዎች ከባለድርሻ አካላት እና ከክልሎች ጋር በሚደረገው ጥረትና መናበብ ያሉ ክፍተቶችን በመለየት የእቅዱን 87 ነጥብ 7 በመቶ መፍታት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራትም የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ተደራሽነትን ከማሳደግ አንጻር ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች 145 ኪሎ ሜትር መስመር በመዘርጋት 59 ኢንዱስትሪዎች የአዲስ ኃይል እና ተጨማሪ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ማለታቸውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃ አመላክቷል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ሰብስቴሽኖች አቅም መሙላት እንዲሁም ኢንዱስትሪዎቹ የሚያቀርቡት የኃይል ፍላጎትና አጠቃቀም አለመመጣጠን፣ የተሰጣቸውን የኃይል መጠን በአግባቡ አለመጠቀም እና የነባር ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች አመሰራረት በኢንዱስትሪ ዞን የተጠቃለለ አለመሆን በኤሌክትሪክ መሰረት ልማት ግንባታ እና ማሻሻያ ላይ ተግዳሮት መሆኑንም አመላክተዋል፡፡