ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ ወሳኝ ነው -መንግስት

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት

ሚያዝያ 25/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያን ወደተሻለ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ኢትዮጵያን ወደተሻለ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፤

ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ ሃገራችን በርከት ያሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትንና ሁነቶችን አስተናግዳለች። የስቅለት፤ የፋሲካ፤ የታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር፤ የኢድ አልፈጥርና የፍቼ ጫምባላላ በዓላት እንዲሁም አለም አቀፍ የሰራተኞች ቀንን ያስተናገድንበት ሳምንት ነበር።

በዚሁ ወቅት በጎንደር ከተከሰተው አሳዛኝ ጥፋት እንዲሁም እሱን ተከትሎ በሌሎች አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከታየው ፍጹም ከኢትዮጵያዊነት ስነምግባር ያፈነገጠ ወንጀል ባሻገር በዓላቱ በመላ ሃገሪቱ በድምቀት ተከብረዋል። በዚህም በዓላቱ ኢትዮጵያውያን በፈተና ውስጥ ይበልጥ የሚጸና የአብሮነት እሴት እንዳላቸው ያሳዩበትና የሃገርንም ገጽታ ለመገንባት ያስቻሉ ናቸው።

በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ያሳተፉት እነዚህ በአላት ከሃይማኖታዊ አስተምህሮታቸው ርቀው የጥፋት ማስተናገጃ እንዲሆኑ ለማድረግና  በኢትዮጵያውያን መካከል የተዘረጋውን የአብሮነት ገመድ ለመበጠስ ያቀዱ ወንጀለኞች ብዙ ጥፋትን ለማድረስ በብርቱ የሞከሩበትም ወቅት ነው።

ይህ ውጥናቸው ባሰቡት የጥፋት ልክና ባቀዱት የወንጀል ስፋት መጠን እንዳይሳካ ላደረጉት ኢትዮጵያውያን በሙሉ መንግስት ከፍ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል። ህዝብ የሰጣቸውን ከፍተኛ ሃላፊነት በጠንካራ ቅንጅትና እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ በመክፈል የተወጡ መላው የጸጥታ አካላትና ተባባሪ ተቋማትም ምስጋና ይገባቸዋል።

ከሰሞኑም በሃይማኖት ሽፋን በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ሁከቶችና ወንጀሎች ላይ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን የፌደራል ፖሊስ፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር እያዋሉ ይገኛሉ። ተጠርጣሪዎቹም ተገቢውን ፍርድ እንዲያገኙ ይደረጋል። ለዜጎች በሰላም መኖር ስጋትን የሚፈጥሩ፤ በሃገር ህልውና ላይም አደጋን የሚደቅኑ አካላት ላይ መንግስት መውሰድ የጀመረውንም እርምጃ በተጠናከረ ሁኔታ ይቀጥላል።

በዚህ ሂደት ለጽንፈኝነትና አክራሪ አመለካከት ቦታ እንደሌለው በተግባር ያረጋገጠው መላው ህዝብ ከሰሞኑ እንደታየው ወንጀለኞችን አጋልጦ በመስጠትና ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ያሳየውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ሚያዝያ 25፣2014 ዓ.ም

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!