ፈተናዎች በፅናት በመሻገር ለመጪው ትውልድ ነጻ፣ ሰላማዊ እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማውረስ ዳር እስከዳር አንድነትን ማጥበቅ ይገባል – ም/ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን

ሚያዝያ 27/2014 (ዋልታ) እንደሀገር የገጠሙንን ፈተናዎች በፅናት በመሻገር ለመጪው ትውልድ ነጻ፣ ሰላማዊ እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማውረስ ዳር እስከዳር አንድነታችንን ማጥበቅ እና መጠበቅ ይገባናል ሲሉ  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስገነዘቡ።

ሚኒስትሩ 81ኛው የአርበኞች ቀን መታሰቢያ በዓል አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-

ለመላው የሀገራችን ሕዝብ!

ለ81ኛው የአርበኞች ቀን መታሰቢያ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፤ አብሮ አደረሰን።

የአርበኞች ቀንን በልዩ ትኩረት እና ክብደት የምንዘክረው ጀግኖች አርበኞች ለሀገር አንድነት እና ሉዓላዊነት መከበር የከፈሉትን ዋጋ በትውልዱ ዘንድ ተምሳሌታዊ የድል አድራጊነት መንፈስ እንዲጋባ በማሰብ ነው።

ታሪክ በከፍታ እንደሚገልጸው ጀግኖች አርበኞች በእናት ሀገር ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን በመመከት እና በጠላት ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ አኩሪ ድሎችን ተቀዳጅተው ነፃና ሉዓላዊት ሀገር አስረክበዋል።

በተለይ ጀግኖች አርበኞች ሀገራችንን ከወራሪ ጠላት ለመጠበቅ በዱር በገደል በመዋደቅ እና አኩሪ ገድል በመፈጸም በትውልድ ቅብብሎሽ የድል አድራጊነት ዘላቂ ፈለግ አውርሰው አልፈዋል።

በዚህ ረገድ ዘንድሮ ለ81ኛ ጊዜ በኩራት የምንዘክረው “የአርበኞች ቀን”  ሀገራችን ያለችበት አኹናዊ ኹኔታ ተከትሎ፤ ለትውልዱ የሚቸረው ታሪካዊ ትርጉም በእጅጉ የተለየ ያደርገዋል።

በአኹን ጊዜ በመላው ሀገሪቱ ሰላም እና ፀጥታን በዘላቂነት ከማስፈን አኳያ ለጀመነው ትግል የቀደሙ ጀግኖቻችንን የድል አድራጊነት ፅኑ መንፈስ ለትውልዱ በማውረስ ረገድ ታሪካዊ ፋይዳው እጅግ የላቀ ነው።

እንዲሁም በዜጎቻችን ላይ የተጋረጡ ማኅበረ~ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን የሚያቀሉ የልማት ውጥኖቻችን በፍጥነት ለማረጋገጥ ከጀመርነው ኹሉአቀፍ ርብርብ አኳያ፤ “የአርበኞች ቀን” የሚያላብሰን ተምሳሌታዊ ትጋት እና ወኔ በልዩነት እና በከፍታ የሚታይ ነው።

እንደሀገር የገጠሙንን ፈተናዎች በፅናት በመሻገር ለመጪው ትውልድ ነጻ፣ ሰላማዊ እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማውረስ ዳር እስከዳር አንድነታችንን ማጥበቅ እና መጠበቅ ይገባናል።

በዚህ አጋጣሚ የቀደሙ ጀግኖቻችንን የድል አድራጊነት ታሪክ፤ ዘመኑ በሚጠይቀን የትግል አውድ ላይ ለመድገም ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ፅናት በጋራ እንድንቆም አደራ ለማለት እወዳለሁ።

መልካም የድል በዓል!