በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን በ90 ሚሊየን ብር የልማት ፕሮጀክቶች እየተሰሩ ነው

ሚያዝያ 28/2014 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ዋጫሌ ወረዳ በ90 ሚሊየን ብር 32 ፕሮጀክቶች እየተሰሩ መሆናቸው ተገለጸ፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን ዋጫሌ ወረዳ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት ሰጪ የሆኑ በርካታ የልማት ሥራዎች በስፋት እየተሰሩ መሆናቸው ተነግሯል።
ወረዳው በአሸባሪው ሸኔ ለሚደርሱ ፈተናዎችና ትንኮሳዎች ሳይንበረከክ ለማኅበረሰብ አገልግሎት ሰጪ የሆኑ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የዋጫሌ ወረዳ ምክትል አስተዳደሪ አበራ ቦጋለ ለዋልታ ተናግረዋል።
በ90 ሚሊየን ብር በጀት 32 የሚሆኑ የልማት ፕሮጀክቶች እየተሰሩ መሆናቸውን ነው የገለጹልን።
በወረዳው የተጀመሩት ፕሮጀክቶች ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቁ የአከባቢው ማኅበረሰብ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ ከመሆኑም ባሻገር ለምጣኔ ሃብታዊ እድገትም አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በወረዳው እየተሰሩ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች የጉምቢቹ-አኖ ባቦ የመንገድ ሥራ ተጠቃሽ ሲሆን በ16 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በጀት የተሠራ ነውም ተብሏል።
መንገዱ 8 ነጥብ 5 ኪ.ሜ እርዝመት ያለው ሲሆን 15 ሺሕ ለሚሆኑ የአከባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት እንደሚሰጥም ተጠቁሟል።
በመንገድ እጦት ሳብያ ለብዙ አመታት ስንፈተን ቆይተናል የሚሉት በወረዳው የዋበሪ ቀበሌ ነዋሪዎች ይህ መንገድ እንዲሰራላቸው ለብዙ ጊዜያት ሲጠይቁ መሰንበታቸውንም ተናግረዋል።
ይሁንና አሁን ጥያቄያቸው መልስ በማግኘቱ ሲደርስባቸው ከነበረው እንግልት መገላገላቸውንም ተናግረዋል።
ታምራት ደለሊ (ከኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን)