የአለም አቀፍ የእሳት አደጋ ተከላካይ ሠራተኞች ቀን ተከበረ

ሚያዚያ 28/2014 (ዋልታ) የአለም አቀፍ የእሳት አደጋ ተከላካይ ሠራተኞች ቀን በአዲስ አበባ ተከብሯል፡፡

የዓለም አቀፍ የእሳት አደጋ ተከላካይ ሠራተኞች ቀን በእሳት አደጋ ሥራ ላይ ተሰማርተው ሳለ በተከሰተዉ የእሳት አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ለማሰብ የሚከበር ነው፡፡

ዘንድሮ በዓለም ዓቀፍ ለ24ተኛ ጊዜ በአገራችንና በከተማችን ለመጀመሪያ ጊዜ የእሳት አደጋ ተከላካይ ሠራተኞች ቀን በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡

በዓሉ በ26/08/2014 ዓ.ም በከተማችን አዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የተከበረ ሲሆን በከተማ ደረጃ በፓናል ውይይት ፣በእግር ጉዞና በፎቶ ዐውደ ርዕይ በደመቀ ሁኔታ በቀን 27/08/2014 ዓ.ም ሙሉ ቀን ተከብሯል፡፡

በፓናል ውይይቱ ላይ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰለሞን ፍስሀ  ባለፉት 88 ዓመታት የኮሚሽኑ  የስራ ዘመናት ታሪክ ውስጥ የእሳት አደጋ ተከላካይ ሰራተኞች የሰዎች ህይወት እና ንብረት ከጉዳት በማዳን የከፈሉት ዋጋ ሁሌም ሲታወስ የሚኖር ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ይህ ዕለት የሌሎችን ሂይወትና ንብረት ለማዳን ዋጋ የከፈሉና እየከፈሉ ያሉ ጀግኖችን የምናስብበት ቀን ነው ብለዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ ከተሳታፊዎች በተነሱ ሀሳቦችና ዕለቱን አስመልክቶ ከመድረኩ የማጠቃለያ ሃሳብ የተሰጠ ሲሆን ይህ ዕለት በየዓመቱ እየተከበረና ለጀግኖች ዕውቅና እየተሰጠ መቀጠል አለበትም ተብሏል፡፡

አደጋን በመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለነበራቸውና አደጋ በመከላከል ስራ ላይ ሳሉ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰራተኞች የሽልማት አሰጣጥ መርኃግብር መከናወኑን የኮሚሽኑ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት መረጃ አመላክቷል፡፡