ሚኒስቴሩ የግብርናውን ዘርፍ አበረታች ውጤቶችን ለማጠናከር በበጀት ሊደግፍ ነው


ሚያዚያ 28/2014 (ዋልታ)
የገንዘብ ሚኒስቴር በግብርናው ዘርፍ የታዩ አበረታች ውጤቶችን ለማጠናከር በበጀት እንደሚደገፍ ገለጸ፡፡
ለሶስተኛ ቀን ቀጥሎ በዋለው የፌዴራል ባለበጀት መስሪ ቤቶች የበጀት ስሚ መርኃ ግብር የግብርና ሚኒስቴርና በስሩ የሚገኙ ተጠሪ ተቋማት የ2015 በጀት ዓመት የበጀት ዕቅድ ያቀረቡ ሲሆን በግብርናው ዘርፍ የታዩ አበረታች ውጤቶችን ለማጠናከር ተገቢው የበጀት ድጋፍ እንደሚደረግም ተገልጿል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የግብርናውን ዘርፍ ለማጠናከር የበጀት ድጋፍ አንደሚደረግ አመልክተው ግብርና ሚኒስቴር ለምግብ ዋስትና ሥራ ለ2015 በጀት ዓመት የጠየቀው ገንዘብ ከተሰጠው ጣሪያ ከፍ ያለ በመሆኑ የበጀት ጥያቄው በተቀመጠው የበጀት ጣሪያ መሰረት እንዲስተካከል አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
የገንዘብ ሚንስትር ዲኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው በግብርና ዘርፍ ከዚህ ቀደም የሚገባውን ያህል ትኩረት እንዳላገኘ ጠቁመው አሁን ላይ የተገኙ ተጨባጭ ለውጦችን ለማጠናከርና ለማስፋፋት መንግሥት ያለውን ውስን ሀብት ጥቅም ላይ ያውላል ብለዋል፡፡