በቦረና በደረሰው ድርቅ ከ1 ሚሊዮን በላይ እንስሳት ሕይወት አልፏል

ሚያዝያ 29/2014 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በደረሰው ድርቅ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የቁም እንስሳት ህይወት ማለፉን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢንስቲትዩት የግብርና ትራንስፎርሜሽን አስተባባሪ ዶክተር ሳሙኤል ቱፋ ፤ የሞቱት እንስሳት ቁጥር ከአንድ ወር በፊት በአካባቢው ዝናብ መጣል ከመጀመሩ በፊት በተሰበሰበው መረጃ መሰረት የተገኘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዝናብ መጣል ከጀመረ አንስቶም ቢሆን የድርቁ ተጽእኖ በመኖሩ የተነሳ ተጨማሪ የቤት እንስሳት ህይወት ሊያልፍበት የሚችልበት ዕድል መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ካሏት የቀንድ ከብቶች መካከል በቦረና የሚገኙት የከብቶች ዝርያዎች ለኢንቨስትመንትም በይበልጥ ተመራጭ ናቸው። አሁን ግን በድርቁ ምክንያት እንስሳቱ በመሞታቸውና ሌሎቹም በመጎዳታቸው በአገር ሃብት ላይ እየደረሰ የሚገኘው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑንም ለኢፕድ ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል በደረሰው ድርቅ ሳቢያ ከ14 ሚሊዮን በላይ እንስሳት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የቁም እንስሳት ሕይወታቸው ሲያልፍ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ በመኖ እጥረት የተነሳ በመዳከማቸው በሰው ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን የኦሮሚያ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መግለጹ ይታዋሳል፡፡