አዲሱ የአባይ ድልድይ የዛሬውን ትውልድ አሻራ ለመጭው የሚያስተላለፍ ነው ተባለ

ሚያዝያ 30/2014 (ዋልታ) አዲሱ የአባይ ድልድይ የዛሬውን ትውልድ አሻራ ለመጭው ትውልድ በማስተላለፍ በታሪክ ሲዘከር የሚኖር ፕሮጀክት መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ገለፀ።
በባህር ዳር ከተማ ዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው አዲሱ የዓባይ ድልድይ በአይነቱ ልዩ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዘርፉ ለተሰማሩ የፕሮጀክት አመራሮችና ሰራተኞች የእውቀት ሽግግር እያስገኘ መሆኑም ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የፕሮጀክት አመራሮችና ሠራተኞች ተጎብኝቷል።
በአስተዳደሩ የመንገድ ሀብት ሲስተም ማኔጅመንት ዳይሬክተር አብርሃም አብደላ እንዳሉት የድልድዩ ግንባታ ከዲዛይን ጀምሮ እስከ ፕሮጀክት ትግበራ ድረስ ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ እየተተገበረ የሚገኝ ነው።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከ5 ሺሕ በላይ ድልድዮችንና ከ40 ሺሕ በላይ ካልበርቶችን የሚያስተዳድር ቢሆንም የዓባይ ድልድይ ፕሮጀክት ግን የተለየ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህ ፕሮጀክት በሌሎች ፕሮጀክቶች ለተመደቡ አመራሮችና ሰራተኞች አዳዲስ እውቀት፣ ልምድና ተሞክሮ የሚያስገኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሀገራችን በድልድይ ግንባታና አስተዳደር ዘርፍ የእውቀት ሽግግር በማምጣት በቀጣይ ሌሎች የዓለም ሀገሮች የደረሱበት የእድገት ደረጃ ለመድረስ በር የሚከፍት መሆኑንም አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱ የባህር ዳር ከተማን ገፅታ በመገንባት የቱሪስት መስህብ በመሆን የሚያገለግል መሆኑን በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የፕሮጀክቱ ቡድን መሪ አዲስህይወት ታደሰ ገልጸዋል።
ድልድዩ 380 ሜትር ርዝመትና 43 ሜትር የጎን ስፋት ያለው በመሆኑ በአንድ ጊዜ ስድስት ተሽከርካሪዎችን፣ የብስክሌትና የእግረኛ መንገድን አካቶ እየተገነባ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከድልድዩ በተጨማሪ 51 ሜትር ስፋት ያለው የ5 ኪሎ ሜትር የመዳረሻ መንገድ ግንባታን፣ የድልድይ ላይ መብራቶችና የትራፊክ ምልክቶችን ያካተተ ዘመናዊ ፕሮጀክት እንደሆነ ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 61 ነጥብ 5 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን፤ በአንድ ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
አዲሱ የዓባይ ድልድይ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት በዓለም አቀፉ የቻይና ኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ እየተከናወነ የሚገኝ ፕሮጀክት ነው።