በክልሉ የሙቀት መጠን በመቀነሱ የመንግስት የስራ ሰዓት ማሻሻያ ተደረገ

ግንቦት 1/2014 (ዋልታ) በጋምቤላ ክልል የሙቀቱ መጠን እየቀነሰ በመምጣቱ የመንግስት የስራ ሰዓት ወደ መደበኛ የስራ ሰዓት መቀየሩን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ፒተር ሆው እንደገለጹት፤ የሙቀቱ መጠን ቀንሶ ለስራ ምቹ ሆኗል።

በመሆኑም የክልሉ መንግስት የስራ ሰዓት ከዛሬ ግንቦት 01 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ቀድሞው ተቀይሯል።

በለውጡ መሰረትም ላለፉት ሶስት ወራት ከጧቱ 1 ሰዓት እስከ 5 ሰዓት ከ 30 የነበረው ከ1 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት ከ30 እንዲሆን ተወስኗል።

እንዲሁም ከሰዓት በኋላ ከ10 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ከ30 የነበረው ከ9 ሰዓት እስከ 11 ሰዓት ከ30 ሆኖ በቀድሞው የመደበኛ የስራ ሰዓት እንዲለወጥ ተደርጓል።

በመሆኑም የክልሉ የመንግስት ሰራተኛ በተጠቀሰው ጊዜ ወደ ቢሮ በመግባት የተለመደ ሥራውን እንዲያከናን ጽህፈት ቤቱ ማስታወቁን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ሜትዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የጋምቤላ ክልል የሜትዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል ጊዜያዊ ዳይሬክተር ተስፋሁን ዓለሙ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት የክልሉ ዕለታዊ አማካይ ከፍተኛ የሙቀት መጠን 31 ዲግሬ ሼልሲየስ ነው።

እንዲሁም የሌሊቱ የሙቀት መጠን ደግሞ 17 ዲግሬ ሼልሲየስ መድረሱን ጠቁመው፤ ባለፉት ሶስት ወራት የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን 42 ነጥብ 5 የለሊቱ ደግሞ 26 ዲግሬ ሼልሲየስ ደርሶ እንደነበር ገልጸዋል።

በክልሉ ሞቃታማ ወራት የሚባሉት የካቲት፣ መጋቢትና ሚያዚያ ወራት ሲሆኑ በእነዚህ ወራት ውስጥ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን እስከ 45 ዲግሬ ሼልሲየስ የሚደርስበት ጊዜ እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ።