በዋግ ኽምራ ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለጤና ተቋማት የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

ግንቦት 1/2014 (ዋልታ) ዩ.ኤስ.ኤይድ ትራንስፎርም ፕራይሜሪ ሄልዝ ኬር ፓዝ ፋይንደር በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለተዘረፉ የጤና ተቋማት 10 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
በኢትዮጵያ የዩ.ኤስ. ኤይድ ትራንስፎርም ፕራይሜሪ ሄልዝ ኬር ፕሮጀክት ኃላፊ እና ፓዝ ፋይንደር ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መንግስቱ አስናቀ እንዳሉት ፕሮጀክቱ የእናቶችና ህፃናት ጤና ለማስጠበቅ በትኩረት እየሰራ ነው።
በዚህም በጦርነቱ ምክንያት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ለወደሙ የጤና ተቋማት ቀደም ሲል 20 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ለ20 ጤና ጣቢያዎችና ለ3 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች የሚውልና 6 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።
ድጋፉም የእናቶች ማዋለጃ፣ የህሙማን መተኛ፣ የቤተ ሙከራና ሌሎች ቁሳቁስ ያካተተ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ3 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የመኝታ ፍራሽ፣ የማብሰያ ቁሳቁስ፣ አንሶላ፣ ብርድ ልብስና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፈ ተደርገዋል።
በቀጣይም በአማራ ክልል የወደሙ የጤና ተቋማትን አገልግሎት ለመመለስና ለማጠናከር 123 ሚሊየን ብር በመመደብ የህክምና ቁሳቁስ ለመደገፍ እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪና የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ሹመት ጥላሁን ፓዝ ፋይንደር የወደሙ የጤና ተቋማት መልሰው እንዲያገግሙ ማድረጉን ገልጸዋል።
ይህም ድርጅቱ ለኅብረተሰቡ የጤና ህክምና አገልግሎት ተደራሽነት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
በዛሬው እለትም ከህክምና ቁሳቁስ በተጨማሪ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው ለዚህም ብሔረሰብ አስተዳደሩ ምስጋና ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ኪዳት አየለ በበኩላቸው ድርጅቱ ወደ ብሔረሰብ አስተዳደሩ ከተሰማራ ወዲህ የጤና ተቋማትን የግብዓት አቅርቦት እያቃለለ ነው።
የሽብር ቡድኑ በብሔረሰብ አስተዳደሩ በፈፀመው ወረራ ምክንያት ከ400 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የጤና ተቋማት ውድመት ማድረሱን ጠቅሰው ፓዝ ፋይደርን ጨምሮ ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ያደረጉት ድጋፍ ከወደመው ንብረት አንፃር 10 በመቶውን ያህል ነው።
በመሆኑም የህክምና ተቋማት በተሻለ ደረጃ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።