ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ በጋራ ለመሥራት ተስማሙ

ግንቦት 2/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት በባዮ ቴክኖሎጂ፣ በህዋ ሳይንስ እና በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ ዙሪያ በጋራ ለመሥራት እንደሚያስችላቸው ተገልጿል።

እስከ 2025 (እ.አ.አ) የሚቆየው ስምምነቱ የሰው ኃይል ሥልጠና፣ የባለሙያ ልውውጥ፣ በኢኖቬሽን ‘ስታርትአፕ’ እና በሌሎች የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፎች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል።

መስከረም ወር ላይ የተቋቋመው የሁለቱ ሀገራት የቴክኒክ ኮሚቴ ያዘጋጀውን የትብብሩን ዝርዝር ተግባራት ስምምነት በኢትየጵያ በኩል የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) እና በደቡብ አፍሪካ በኩል ደግሞ የሳይንስ እና ኢኖቬሽን ዲፓርትመንት ተወካይ ዳን ዱ ቶይት ፈርመውታል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በህዋ ሳይንስ፣ በምርምር እና በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ ደቡብ አፍሪካ ያላትን የተሻለ ልምድ ትወስዳለች ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።