የክልል ርዕሰ መሥተዳድሮችና ሚኒስትሮች ባሕር ዳር ገቡ

የክልል ርዕሰ መሥተዳድሮች

ግንቦት 3/2014 (ዋልታ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ የክልል ርዕሰ መሥተዳድሮች እና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የአማራ ክልል መንግሥት ባዘጋጀው በሕግ ማስከበርና በኅልውና ዘመቻ ለተሳተፉ የጸጥታ አካላት የዕውቅና መርኃ ግብር ላይ ለመሳተፍ ባሕር ዳር ገብተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ጌታቸው ጀምበር (ዶ/ር) እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በባሕር ዳር በላይ ዘለቀ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው አቀባበል አድርገውላቸዋል።

አሸባሪው ትሕነግ ሀገር ለማፍረስ የከፈተውን ጦርነት ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን በማጠናከር የጥፋት መንገዱን አክሽፈዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት ባዘጋጀው የምሥጋናና የእውቅና መርኃ ግብር ለጸጥታ አካላት፣ ግለሰቦችና ተቋማት የዕውቅና መርኃ ግብሩ ትናንት የተጀመረ ሲሆን ዛሬም በሕግ ማስከበርና የኅልውና ዘመቻ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ መከላከያ፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፖሊስ፣ ፋኖ፣ ሚሊሻና የክተት ጥሪ ተሳታፊ የሕዝብ ኃይል ዕውቅና ይሰጣል።

ከሽብርተኛው ሕወሓት ጋር ሲፋለሙ በጀግንነት የተሰውትም ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት በክብር ዕውቅና ይሰጣቸዋል ተብሏል።

በዘመቻው የተሳተፉ ተቋማት፣ ባለሃብቶች፣ የብዙኃን መገናኛዎችና ሌሎች አደረጃጀቶችም ዕውቅና ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የክልል ርዕሰ መሥተዳድሮችም ኢትዮጵያን ለማዳን በተደረገው ዘመቻ ላደረጉት አስተዋጽኦ ዕውቅና እንደሚሰጣቸው የአሚኮ ዘገባ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW