ኩባ ለኢትዮጵያ ለምታደርገው ድጋፍ ምስጋና ቀረበላት

ግንቦት 3/2014 (ዋልታ) በኩባ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ገነት ተሾመ የሹመት ደብዳቤ ቅጂያቸውን ለኩባ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሊዮ ሮድሪገዝ ፔርዶሞ አቅርበዋል።
አምባሳደር ገነት ኩባ በተባበሩት መንግሥታት መድረኮች ለኢትዮጵያ ለምታደርገው ያላሰለሰ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አምባሳደሩ በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎችና የአፍሪካ ቀንድን በሚመለከቱ ጉዳዮች በተለይም የኅዳሴ ግድብን እና የሦስተኛውን ዓመት ሙሌት አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሊዮ በበኩላቸው የኢትዮጵያ እና ኩባ ወዳጅነት ጥንታዊና ታሪካዊ መሆኑን በማውሳት በኩባ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ በመቃወም ኢትዮጵያ ላሳየችው ያልተቋረጠ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ እና ኩባ ግንኙነት ወደፊት ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!