በመዲናዋ 1 ሺሕ 587 ኢንተርፕራይዞችን ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ማሸጋገር መቻሉ ተነገረ

ግንቦት 4/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንተርፕራይዞችን ማደራጀት ከተጀመረ ጌዜ አንስቶ በአስር ዙሮች 1 ሺሕ 587 ኢንተርፕራይዞችን በማስመረቅ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ማሸጋገር መቻሉ ተነግሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ “የኢንተርፕራይዞች ሽግግር ለኢንዱስትሪ መሠረት” በሚል መሪ ቃል ከ11ኛ ዙር ተመራቂ ኢንተርፕራይዞች፣ ከተቋማት እና ኢንቬስተሮች ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል።
ውይይቱም ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ለተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ ኢንዱስትሪያሊስት እንዲሆኑ የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ ነው።
በዚህም የዘርፉን ችግር ለመፍታት እና ምርታማነትን ለማሳደግ በየደረጃው የኢንተርፕራይዞች ሽግግርን ለማከናወን ቢሮው ለኢንተርፕራይዞች ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ የእድገት ሽግግር እያከናወነ መሆኑም ነው የተገለጸው።
በተያዘው አመትም መስፈርቱን ያሟሉ 179 ኢንተርፕራይዞች ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ መሸጋገራቸው ተገልጿል።
በመዲናዋ በአሁኑ ጊዜ ከ36 ሺሕ በላይ ኢንተርፕራይዞች እና ኢንዱስትሪዎች፣ ከ90 ሺሕ በላይ አንቀሳቃሾች እንዳሉም ተጠቁሟል።
በእመቤት ንጉሴ