ኢትዮጵያና ቻይና የኢንቨስተመንትና ንግድ መግባባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

ግንቦት 4/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ከቻይና መንግሥት ጋር በኢንቨስትመንትና ንግድ ልማት ዙሪያ በጋራ መስራት የሚያስችል የመግባባቢያ ስምምነት ተፈራረመች፡፡

ስምምነቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሚ እና በቻይና ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ዳሬይክተር ያንግ ዩሀንግ ተፈርሟል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ስምምነቱን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በማድረጓ ከጊዜ ወደ ጊዜ የውጭ ኢንቨስትመንት ስበት ማዕከል እየሆነች ነው።

በዚህም በሀገራችን ኢንዱስትሪን ከማስፋፋት አኳያ የቻይና መንግሥት በኢንቨስትመንት ዘርፉ ዋነኛ አጋራችን ነው በማለት ገልፀዋል።

ቻይና በምስራቅ አፍሪካ በሰላምና ልማት ጉዳዮች ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ትገኛለች ያሉ ሲሆን በኢትዮጵያም ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አጋርነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቁርጠኞች ነን ብለዋል።

ስምምነቶቹ የጤና፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት፣ የግብርና እና የኢንቨስትመንትና ንግድ ትስስርን የሚያጠናክር ነው ተብሏል።

የመግባቢያ ስምምንቱ የቻይና መንግሥት በኢትዮጵያ እየተገነቡ ባሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ እና በንግድና ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ የሚያስችላቸው አዲስ ስምምነት ነው፡፡

ኮሚሸነር ሌሊሴ ነሚ የመግባቢያ ስምምንቱ መፈረም ኢትዮጵያ ለጀመረችው ኢኮኖሚያዊ ግስጋሴ የአቅም ግንባታ እና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡

በደረሰ አማረ