ግንቦት 4/2014 (ዋልታ) ሕንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን ዐቀፍ ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ ገለጹ፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ ኤዥያ እና ፓስፊክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ገበየሁ ጋንጋ እና በኢትዮጵያ የህንድ ኤምባሲ ሰራተኞች የትውውቅ መድረክ በመፍጠር በሁለቱም ሀገራት የሚከናወኑ ሥራዎች በተሳለጠ መልኩ ማስኬድ የሚያስችል ሁኔታዎችን ማመቻቸትና ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮችን አላማ ያደረገ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይታቸው ወቅት አምባሳደር ገበየሁ ጋንጋ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የውስጥ ጉዳዮቻችንን ሁሉን ዐቀፍ ውይይት በማካሄድ ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ የሚያስችል ሰፊ ሥራ እየተሰራ መሆኑንና እና የፌዴራል መንግሥቱ በሀገሪቱ ሰላም ለማስፈን በርካታ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን አብራርተውላቸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደው የተኩስ አቁም ውሳኔ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን ገልፀው በታላቁ የኅዳሴ ግድብና በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ ዙሪያ በማብራራት ኢትዮጵያ ጉዳዩ በውይይትና በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለበት ብላ እንደምታምን ገልፀውላቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳዳር ሮበርት ሼትኪንቶንግ በበኩላቸው አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እንደሚረዱና አገራቸውም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን ዐቀፍ ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል፡፡
ከ
ንግድና ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን በማንሳት የትውውቅ ሰብሰባው በእንጥልጥል ላይ ያሉ ጉዳዮችን በጋራ ለማየትና መፍትሔ ለማስቀመጥ ጠቃሚ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ጠንካራ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ቁርጠኛ መሆናቸውን መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።