ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያ ምቹ የዲጂታል ስነ ምህዳር እየፈጠረች መሆኑን አስታወቀ

ግንቦት 5/2014 (ዋልታ)) ኢትዮጵያ ምቹ የዲጂታል ስነ ምህዳር እየፈጠረች በመሆኑ አለም አቀፍ ተቋሟት በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው 19ኛው የኢኖቬሽን አፍሪካ ዲጂታል ጉባኤ ተጠናቋል።

የዲጂታል ይዘትና አገልግሎት ላይ ትኩረቱን አድርጎ በተካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ ከ26 በላይ ድርጅቶችና ከ390 በላይ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ተሳታፊዎች ታድመዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ምቹ የዲጂታል ስነ ምህዳር እየፈጠረች በመሆኑ አለም አቀፍ ተቋሟት በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።

በቴሌኮም ዘርፍ የተጀመረው ማሻሻያ ለዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራው ትልቅ አቅም ይፈጥራል ያሉት ሚኒስትሩ አጋር አካላት እንዲሁም አለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ድርጅቶች የኢትዮጵያን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የሚያግዙ የዲጂታል ይዘትና አገልግሎቶች ላይ እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።

ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው ይዘቶችና እና አገልግሎት ላይ ለሚሳተፉ አካላት መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡