መንግሥት አልሻባብ በመሃል ሀገር ሊፈጥር ያቀደውን ሽብር ማክሸፉን ገለጸ

ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

ግንቦት 6/2014 (ዋልታ) መንግሥት አልሻባብ ከአሸባሪዎቹ ሕወሓት እና ሸኔ ጋር በጥምረት በመሆን በመሃል ሀገር ሊፈጥር ያቀደውን ሽብር በወሰደው እርምጃ ማክሸፉን ገለጸ፡፡

እስካሁን በተደረገው ክትትልና ቁጥጥር 45 ተላላኪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

በርካታ የጦር መሳሪያዎች ተይዘዋል ያሉት ሚኒስትሩ በዚህም 105 ክላሽ እንኮቭ ጠመንጃ፣ 13 ብሬል፣ 4 መትረዬስ እና 4 ስናይፐር መሳሪያዎች በቤተ እምነትም ውስጥ ጭምር መያዛቸውን ጠቁመዋል፡፡

የተጎዱ መስጊዶችንና አብያተክርስቲያናት መልሶ ለመገንባት መንግሥት ወደ ሥራ መግባቱንም ገልጸዋል፡፡

የተጠረጠሩ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

በአማራ ክልል ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ህግ በማስከበርና ክልሉን ወደ ተረጋጋ እንቅስቃሴ ለመመለስ ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ የሚያደርግ ሀሳብ ተነድፎ ወደ ተግባር እንደተገነባም አመልክተዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በአሸባሪው ሸኔ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ ቀጥሏል ያሉት ሚኒስትሩ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የአሸባሪው ሰራዊት መደምሰሳቸውንና ማሰልጠኛ ቦታዎችም መፍረሳቸውን እንዲሁም መሳሪያዎች መማረካቸውን ተናግረዋል፡፡

መንግሥት በአሸባሪዎች እና በህገወጦች ላይ የሚወስደውን እርምጃ ባልተገባ መልኩ በመተርጎም የተዛባ መረጃ ለማኅበረሰቡ የሚያደርሱ ጽንፈኛ ሚዲያዎች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባልም ብለዋል ሚኒስትሩ በመግለጫቸው፡፡