ሕወሓት ለዳግም ጦርነት ዝግጅቱ ከስህተቱ አለመማሩን የሚያረጋግጥ ነው

                                             የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

ግንቦት 6/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓት በትግራይ አጎራባች ክልሎች ዳግም ወረራ ለመፈፀም እያደረገ ያለው ዝግጅት ከስህተቱ አለመማሩን እና በፀረ-ሕዝብነቱ መቀጠሉን የሚያረጋግጥ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

ለትግራይ ክልል ሕዝብ ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዳይሆን አሸባሪ ቡድኑ ለማስተጓጎል የሚያደርገውን ሰብአዊነት የጎደለው ተግባር እንዲያቆም ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ጫና እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ለዳግም ጦርነት በግልጽ እየተዘጋጀ መሆኑን ዓለም ዐቀፍ ጋዜጠኞች ጭምር እያጋለጡ መሆኑን ጠቅሰው “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል እወርዳለሁ” የሚል የጥፋት አጀንዳውን ቀጥሎበታል ብለዋል።

የሰብአዊ ድጋፍና የግብርና ሥራ እንዳይስተጓጎል መንግሥት ያወጀውን የተኩስ አቁም ለዳግም ጥፋት እየተዘጋጀበት መሆኑንም ገልጸዋል።

በአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች መንግሥት የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ በማድረግ ላይ ቢሆንም አሸባሪ ቡድኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች የማስተጓጎል ተግባር ስለመፈጸሙ ጠቅሰዋል።

ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶችም የተሳለጠ ሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ ማድረግ እንዲችሉ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የአሸባሪ ቡድኑ እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ከስህተቱ የማይማርና በፀረ-ሕዝብ ተግባሩ መቀጠሉን ማረጋገጫ ነው ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

በጦርነቱ በተጎዱ አካባቢዎች ለአርሶ አደሩ የዘርና የማዳበሪያ አቅርቦት ተደራሽ በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቁመው በትግራይ አካባቢ ግን ለግብርና ሥራውም ይሁን ለሰብአዊ አቅርቦቱ አሸባሪው ሕወሓት እንቅፋት ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል።