ዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የ15.6 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ ተስማማ

ግንቦት 8/2014 (ዋልታ) ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚውል የ15 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር (300 ሚሊዮን ዶላር) ድጋፍ ለማድረግ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ከኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና የኤርትራ ዳይሬክተር ኦስማኔ ዶኔ ጋር ተፈራርመዋል።

የድጋፍ ስምምነቱ በጦርነቱ በአማራ፣ አፋር፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችና ማኅበረሰብ ለመልሶ ግንባታና መልሶ ማቋቋም ሥራዎችን በአስቸኳይ ለመደገፍ ያለመ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

ድጋፉ በተመረጡ የግጭት ተጎጂ ወረዳዎች የጤና፣ የትምህርትና የውሃ መሰረት ልማት መዘርጋት ብሎም ለፆታዊ ጥቃት የተጋለጡ ሴቶችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም ይውላል ተብሏል።

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የፌዴራል መንግሥት በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት በተያዘው ዓመት 5 ቢሊየን ብር መመደቡን አስታውሰው ለቀጣይ በጀት ዓመትም 20 ቢሊዮን ብር መመደቡን ገልጸዋል።

የዓለም ባንክ ለመልሶ ግንባታ የሚውል ፕሮጀክት ያደረገው የልማት ፋይናንስ ድጋፍ በጦርነቱ ከደረሰው ውድመት አንፃር ከፍተኛ ባይሆንም ለተጎዱ አካባቢዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ግን ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የዓለም ባንክ ድጋፍ በጦርነቱ በድርቅ፣ በኮቪድ-19ና በዓለም ዐቀፍ ክስተት የተጎዳውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለማገዝ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም አመልክተዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW