የሀረሪ ክልል መሬት አጥረው በተቀመጡ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ ሊወስድ ነው

ግንቦት 8/2014 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል መሬት አጥረው በተቀመጡ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ርዕሰ መስተዳድር አርዲን በድሪ ገለፁ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በኢንቨስትመንት ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ለሚያለሙ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ሆኖም ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው ክልሉን ባላለሙ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ ይወሰዳል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ያለው ውስን መሬት በአግባቡ መጠቀምና ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በክልሉ መሬትን አጥሮ ከማስቀመጥ ባሻገር ባለሃብቱ መሬትን ለሌላ አካል ማስተላለፍ እና ከተፈቀደ የኢንቨስትመንት ሥራ ውጪ የመሥራት ችግር እንደሚስተዋል አንስተዋል።
በቀጣይ በተሰማራበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ሊሰራ የሚችል፣ የሥራ እድል የሚፈጥርና ኢኮኖሚውን ሊያነቃቃ ለሚችል ባለሃብት እድል ለመስጠትና ለመደገፍ የክልሉ መንግሥት ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።
ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር)