ህጋዊ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭትን በሚያስተጓጉሉ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገለጸ

ግንቦት 8/2014 (ዋልታ) ህጋዊ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭትን በማስተጓጎል ነዳጅ ለህብረተሰቡ በወቅቱ እንዳይደርስ በሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ምክክር በሚኒስቴሩ ተካሂዷል፡፡

በምክክሩ ላይ አምባሳደር ግርማ ብሩን ጨምሮ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት፣ ከንግድ ቢሮዎች፣ ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት፣ ከኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጅ ባለስልጣን እንዲሁም ከነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ዙሪያ የተስተዋሉ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ያሳለፍነው ሚያዚያ ወር የትንሳኤ በዓል እና 1443ኛው የኢድ በዓል የተከበሩበት ወቅት በመሆኑ በእነዚህ በዓላት ምክንያት ነዳጅ ከጂቡቲ ወደብ ወደ አዲስ አበባ ባለመጫኑ በተፈጠረ ክፍተት ጊዜያዊ የነዳጅ እጥረት በመከሰቱ በየማደያዎቹ የተሽከርካሪዎች ሰልፍ መስተዋሉ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

በውይይቱ የአቅርቦት ውስንነት፣ የቁጥጥር ስርዓቱ ድክመት፣ ከጅቡቲ አዲስ አበባ ባለው የነዳጅ ማጓጓዝ ሂደት የነዳጅ ቅሸባና የአሽከርካሪዎች በየቦታው ለረጅም ሰዓታት መቆም እንዲሁም መንግስት ከፈቀደው የግብይት ቦታና ዋጋ ውጪ የዋጋ ጭማሪ አድርጎ የመሸጥ ፍላጎት የነዳጅ አቅርቦትና ሥርጭቱን እየፈተኑት ያሉ ችግሮች መሆናቸው ተብራርቷል፡፡

ችግሮቹን በመፍታት ምርቱን ለተጠቃሚው ለማድረስ አሰራርን ከማስተካከል ጀምሮ መንግስት ከዘረጋው የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ሂደት ውጭ በሚፈጽሙ አካላት ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳልም ተብሏል፡፡

እርምጃው ነዳጅ ከጅቡቲ ጭነው ሲመጡ በመተሐራና ሌሎችም ከተሞች ለረጅም ሠዓታት በሚቆሙ አሽከርካሪዎች እና ነዳጅ በወቅቱ ለተጠቃሚው በማያደርሱ ማደያዎች ላይም እንደሚወሰድ የተገለጸ ሲሆን በትክክለኛው መንገድ እየሰሩ ያሉ ማደያዎችና ድርጅቶች ብቻ እንዲቀጥሉ ይደረጋልም ተብሏል፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ ጥናቶችን በማካሄድ በነዳጅ አቅርቦት፣ ሥርጭትና ቁጥጥር ሂደት ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከስምምነት ላይ በመድረስ ምክክሩ መጠናቀቁን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡