የታሪክና የኦሮሞ ባህል ምሁሩ አቶ ስንታየሁ ቶላ አረፉ

ግንቦት 8/2014 (ዋልታ) ታላቁ የታሪክና የኦሮሞ ባህል ምሁር አቶ ስንታየሁ ቶላ ቀናዓ ባደረባቸው ድንገተኛ ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
አቶ ስንታየሁ ቶላ በኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከባለሙያነት እስከ ምክትል ኃላፊነት በሀገር ደረጃ ብሎም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የኦሮሞን ሕዝብ ያስተዋወቀ በርካታ ሥራዎችን የሰሩ ታላቅ ምሁር ነበሩ።
ያደረባቸው ድንገተኛ ህመም እስኪያጋጥማቸውና ለህልፈት እስኪዳረጉ ድረስም የኦሮሞ ጥናትና ምርምር እኒስትቲዩት ምክትል ዳይሬክተር ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።
አቶ ስንታየሁ ለኦሮሞ ሕዝብ ብሎም ለኢትዮጵያ ከፈፀሟቸው ተግባራት መሀከል የገዳ ስርዓት ከማይዳሰሱ የሰው ልጅ ሀብቶች መሀከል እንዲሰፍርና በዩኔስኮ እንዲመዘገብ የአንበሳውን ድርሻ የተወጡ ሰው ናቸው።
የኦሮሞ ሕዝብ በአደዋ ድል፣ በሳምቤና በሌሎች የጣሊያን የድል አውድማዎች በጥናት በማሳየት የኦሮሞ ሕዝብ ለኢትዮጵያዊያን ጋሻ መሆናቸውን አንፀባርቀው ማሳየትም ችለዋል ።
ከገዳ ስርዓት በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ቅርሶች የሶፍ-ዑመር ዋሻ፣ ድሬ ሼክ ሁሴን፣ የባሌ ተራሮች ፓርክና ሌሎችም በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ በእጩነት እንዲቀርቡም ጠንካራ ሥራ ሲሰሩ ቆይተዋል።
የታሪክና የኦሮሞ ባህል ምሁሩ አቶ ስንታየሁ ቶላ የሁለት ልጆች አባት ሲሆኑ ባደረባቸው ድንገተኛ ህመም በዛሬው ዕለት ግንቦት 8/2014 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።