የህግ የበላይነት አለመከበሩ ሀገሪቱ ለገጠማት ችግር መንስኤ ነው ተባለ

ግንቦት 9/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት አለመከበሩ ሀገሪቱ ለገጠማት ችግር በቀዳሚነት የሚጠቀስ ችግር መሆኑን ዋልታ ቴሌቪዥን ያነጋገራቸው የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች ገለጹ፡፡

የአፋር ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሙሳ አብዶ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የሀገሪቱን እድገት ለማፋጠንም ሆነ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ህግን አክብሮ መስራት መፍትሄ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሀገር በተረጋጋ መንፈስ እንድትቀጥል፣ ዜጎቿ በሰላም ወጥተው እንዲገቡና በፈለጉት ቦታ ሰርተው መኖር እንዲችሉ መንግሥት ህግን በማክበር እና በማስከበር በኩል በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ነጅመዲን አልማሀዲ በበኩላቸው እንደ ሀገር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ህግ ማስከበርን መሰረት አድርገው የወጡ ህጎችን መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ለዚህም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም የወጣውን ህግ በአግባቡ በመተግበር እና የዜጎችን መብት በማስከበር ሙያዊ ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ህግን ማስከበር የመንግሥት ድርሻ ብቻ ባለመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እና ዜጎች የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ተብሏል፡፡

በአመለወርቅ መኳንንት