ኤርትራ ሕወሓት ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን አስታወቀች

ግንቦት 10/2014 (ዋልታ) የኤርትራ መንግሥት ሕወሓት ለዳግም ጦርነት በዝግጅት ላይ እንደሆነ በመግለጽ እራሷን ለመከላከል ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች።
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ትላንት ባወጣው መልዕክት ሕወሓት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበር አካባቢና በወልቃይት አቅጣጫ ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጀ መሆኑን በመግለጫው አብራርቷል።
ኤርትራ በሕወሓት ሊሰነዘር ይችላል ላለችው ጥቃት የመጀመሪያው ዒላማ “ኤርትራና የኤርትራ ሕዝብ ናቸው” ብላለች።
ባለፈው ሳምንት የአማራ ክልል የጸጥጣ ምክር ቤት በተመሳሳይ መልኩ ከሕወሓት በኩል ሊሰነዘር ይችላል ላለው ሌላ ዙር ወረራ የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ዝግጁ እንዲሆን ትዕዛዝ ማስተላለፉ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራል መንግሥት ኃይሎች መካከል ውጥረት እየጨመረ መምጣቱን ገልጾ አልፎ አልፎም ግጭቶች ሪፖርት መደረጋቸውን አስታውቋል።
ባለፈው ሳምንት የትግራይ ኃይሎች ከኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ለጥቂት ሰዓታት የቆየ ጥቃት ሰንዝረው የከባድ መሳሪያ ተኩስ ልውውጥ እንደነበረ ቢቢሲ መዘገቡ አይዘነጋም።
በኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ድረ-ገጽ ላይ ትናንት የወጣው ጽሑፍ ላይ ግን ሚያዚያ 30/2014 ዓ.ም ራማና ባድመ አካባቢ ከሕወሓት ኃይሎች ጋር ግጭት አጋጥሞ ነበር ስለመባሉ ያለው ነገር የለም።
ሕወሐት በዓለም ዐቀፍ ሕግ የኤርትራ ሉዓላዊ ግዛት እንደሆነ የተረጋገጠ አካባቢ ዳግም ለመውረር በዝግጅት ይገኛል ሲል ከሷል። ከዚህ በተጨማሪም ሕወሓት ወልቃይት፣ ጠገዴና ሑመራን መልሶ በመቆጣጠር ከሱዳን ጋር በምድር ለመገናኘት ድንበር ለመክፈት አቅዷል ብሏል።
ከሕወሓት ሊሰነዘር የሚችልን ጥቃት የኤርትራ ሕዝብ እና መንግሥት መከላከል ይችላል ማለቱን ቢቢሲ ዘግቧል።
ከኤርትራ ለቀረበው የወረራ ስጋት አስካሁን ሕወሓት በኩል የተባለ ነገር የለም።
ሕወሐት በኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ መሰየሙ ይታወሳል፡፡